በአማራ ክልል የተጀመረው የህዝብ ማመላለሺያ ሾፌሮችና ባለንብረቶች አድማ ለ4ኛ ቀን እንደቀጠለ ነው

ታህሳስ  ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከታህሳስ 22 ቀን ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለዉ የአማራ ክልል የህዝብ ትራንስፖርት ሾፌሮች እና የመኪና ባለንብረቶች የስራ ማቆም አድማ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከባህር ዳር ወደ ጎንደርም ሆነ ወደ ደብረማርቆስ አገልግሎት የሚሰጡ አዎቶቡስና ሚኒባሶ መኪኖች  ባለመኖራቸዉ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ ተውቋል።

የሚኒባስ ሾፌሮች ” መንግስት በእኛ ላይ በመድረስ ላይ ያሉትን ችግሮች በዉይይት ለመፍታት እንዲያነጋግረን በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ወደ ስራ ማቆም እርምጃ ገብተናል” ብለዋል፡፡

አሁን ለተደረገዉ ስራ ማቆም አድማ መነሻ የሆነዉ ሶስት ጊዜ ጥፋት አጥፍቶ የተገኘ አሽከርካሪ ለስድስት ወር መኪና ከማሽከርከር ይታገዳል የሚል በፌደራል መንግስት የወጣዉ ን ህግ የክልሉ መንግስት ለማስፈፀም በሚወስደው ርምጃ የተነሳ ቢሆንም ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ በስርአቱ አራማጆች እየደረሱ ያሉት ችግሮች ከጊዜ ወደጊዜ መጨመራቸዉ ሁኒታዉን ወደ ስራ ማቆም ደረጃ እንደገፋው አሽከርካሪዎች ይገልፃሉ፡፡

የስርአቱ ጠባቂ የሆኑ የትራንስፓርት ተቆጣጣሪዎች ጥፋት ይሁን አይሁን ባልታወቀ ጉዳይ አስከ 500 ብር የመቅጣት መብት ያላቸዉ በመሆኑና በተደጋጋሚ የሚቀጡ በመሆኑ ስራቸዉን ዉስብስብ እናዳደረገዉ ገልፀዋል፡፡

ይህንኑ በመካሄድ ላይ ያለዉን የስራ ማቆም አድማ ጋር ተያይዞ አመፅ ለማስነሳት ቅስቀሳ አድርጋችኃል በሚል የታሰሩ እንዳሉ እና በአናዳዶቹ ላይ ከፍተኛ ማስፈራራት ከመንግስት ባለስልጣናት እየደረሰባቸዉ እንደሆነ እና በሰላም ሰርተዉ የመኖር መብታቸዉ አጠራጣሪ ሁኔታ ላይ እንደወደቀ ተናግረዋል፡፡

በዛሬዉ እለት የክልሉ ርእሰ ብሄር አቶ አያሌዉ ጎበዜ በጉዳይ ላይ እየመከሩ ነዉ የሚባል ነገር ቢኖርም አሽከርካሪዎች ግን ከችግሩ ብዛት የተነሳ ዉይይቱ ብዙም ፋይዳ ይኖረዋል የሚል እምነት እንደሌላቸዉ ገልፀዋል፡፡

በዛሬዎ እለት አንዳድ አሽከርካሪዎች ከባህርዳር አዉቶብስ ማረፌያ ተነስተዉ ወደ ጎንደር እና ደብረታቦር ሲሄዱ ታህሳስ 22 ቀን በስራ ላይ ለመሆናችሁ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካላቀረባችሁ ከባህር ዳር ከተማ መዉጣት አትችሉም መባላቸዉን ገልፀዋል፡፡

በትራንስፖርት ላይ የተፈጠረዉን ችግር ለመፍታት የሽከርካሪዎችን ችግር መመርመርና መነጋገር ሲገባ አሽከርካሪዎች ያቀረቡትን የውይይት ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ጉዳዩን ከፀረ-ልማት ጋር ማያያዝ ተገቢነት የለዉም በማለት ምሬታቸዉን የገለጹ ሾፌሮች መኖራቸውን ከባህርዳር የደረሰን ዜና ያመለክታል።

ኢሳት ባደረገው ማጣራት አንዳንድ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ አሽከርካሪዎች ስራ ለመስራት መኩራ ሲያደርጉ በሌሎች አሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሌሎች የመኪና ባለንብረቶች አድማውን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸውም ታውቋል።