ታህሳስ ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ቃል የተመላለሱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኤርትራ ስልጣን ላይ ካሉ ግለሰቦች መቀያየር ጋር የምታያይዘው አንዳችም ነገር የለም ካሉ በሆላ ዝንባሌው እራሱ ከኤርትራ ባህልና እሴት የሚቃረን መሆኑን ገልጠዋል::
እንነጋገር የሚለው አባባል ምንጩ ከየት እንደሆነ እንረዳልን ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ይህ አይነት አካሄድ ትኩረት ከማስቀየር በቀር ምንም አይነት ጥቅም እንደሌለውና ኤርትራም የምትገባበት ድራማ እንዳልሆነ አመልክተዋል::
የድንበር ኮምሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ ላለመሆኑ የአሜሪካ መንግስት ተጠያቂ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን ከሀገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል::
ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ መንግስት በሀገራቸው ላይ የጣለውን መአቀብ በመቆቆም አንድነቱንና እድገቱን በማጠናከር መዝለቁንም በዚሁ ቃለምልልስ ገልጠዋል::
ከአልቃይዳና ከአልሸባብ የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል የተባሉ 10 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ :: አንዱ በነጻ ተለቀቀ::
በተያያዘ ዜና በሱማሊያ ከሚገኙ እስላማዊ ሀይሎች ጋር ያላቸውና በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተዘጋጁ ያላቸውን 15 ተጠርጣሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት መያዙን ሮይተርስ ዘገበ:፡ የፌደራል አቃቢ ህግ ክስ የመሰረተባቸውና በዕስር ላይ ሆነው ክሳቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት መካከል በሽር ሀጂ እስማኤል የተባለው ተከሳሽ ነጻ ሲወጣ ሌሎች 10 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብልዋል::
አቃቢህግ የወንጀሉ ጠንሳሽ የአልቀኢዳና የአልሸባብ ዋና ተላላኪ ያለውን ነዋሪነቱ በሶማሊያ ሞቃዲሾ የሆነውን ሀሰን ጋርሶ ስቶላ ክሱ እንዲከብድና በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣለት ጠይቆል::
ጥፋተኛ የተባሉት 10 ተከሳሾች በህቡ በመደራጀትና በመንቀሳቀስ በኢትዮጵያ የፖለቲካና የሀይማኖት አላማ ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ህብረተሰቡን በማስፈራራት ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፈራረስ በአሸባሪነት ከተፈረጁት ከአልቃይዳና ከአልሸባብ ጋር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አቃቢ ህግ በክሱ ላይ አስረድቶል::
በዚህ መሰረት ግለሰቦቹ ሊፈጽሙት የነበረው ወንጀል ከባድ እንዲባል አቃቢ ህግ ፍርድ ቤቱን ጠይቆል::
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የደህንነትን የጸጥታ አገልግሎት 20 ሰአት በፈጀ ዘመቻ በሀገሪቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸምምያቀዱ 15 ሰዎችን መያዙን ሮይተርስ ዘግቦል::
እንደዘገባው ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በሱማሊያ ከሚገኝ እስላማዊ ቡድን የተቀጠሩ፡የሰለጠኑና በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የተሰማሩ ናቸው ብሎል የኢትዮጵያ የደህንነትን የጸጥታ አገልግሎት:፡
የተያዙት 15 ሰዎች ዜግነት አልተገለጠም ያለው ሮይተርስ ከሱማሊያና ከኬኒያ አቆርጠው ኢትዮጵያ መግባታቸውን ግን ዘግቦል:፡