ህዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ትናንት ጥቅምት 26/2005 በዳላስ ቴክሳስ የተጀመረው ስብሰባ ዛሬ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ የፃፉት ደብዳቤና ደብዳቤውን በተመለከተ ለቪኦኤ የሰጡት መግለጫ ዐቢይ መነጋገሪያ ሆኖ ወጥቶዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን አለም አቀፍ ማህበር ለተደራዳሪዎቹ አባቶች በላከው ግልፅ ደብዳቤ ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነት ሲሉ በመቻቻልና ሰጥቶ መቀበል መረህ መፍትሄ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ማክሰኞ ከትላንት በስቲ ሕዳር 25/2005 ለብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ በፃፉት ደብዳቤ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፣ ፕሬዚዳንት ግርማ በፃፉት በዚህ ደብዳቤ አዲስ ፓትሪያርክ እንዳይሾም በሀገር ሽማግሌዎችና በምእመናን የሚደረገው ጥረት በርሳቸውም በኩል ተቀባይነት እንዳለውም አመልክተዋል። ፕሬዚዳንቱ መልእክታቸውን ሲያጠቃልሉም የሚከተለውን ጥሪ አቅርበዋል።
“ቅዱስነትዎ ይህን ሀሳብ ተቀብለው ልዩነትን በማጠበብ በቤተክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን በቅዱስነትዎ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ይዘው ወደ አገርዎትና ወደ ቤተክርስቲያንዎ አንዲገቡ ይህን ደብዳቤ ፅፈናል” በማለት ከስማቸው ጋር ፊርማቸውን አያይዘዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ የህንን ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ለፌድራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲያውቁት የላኩ ሲሆን በግልባጭ በኢንጂነር አርጋው ጥሩነህ ለሚመራው የሽመግሌዎች ቡድን አድርሰዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ይህ ደብዳቤ ከርሳቸው የተፃፈ መሆኑን በትናንትናው ዕለት ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ የአማርኛው አገልግሎት አረጋግጠዋል።
በዚህ ቃለ-ምልልስ ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ ከስልጣናቸው ታግደው መነሳታቸውን ይህንንም የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ታምራት ላይኔ መመስከራቸውን እንደተረዱ አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ለቪኦኤ እንደገና በሰጡት ቃለ-ምልልስ ደብዳቤውን ከስልጣናቸው አልፈው የፃፉት በመሆኑ እንደሳቡት ገልፀውል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በከፍተኛ ጉጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን የሚጠበቀው በዳላስ ቴክሳስ የተጀመረው ድርድር ዛሬ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎዋል።
ይህ ድርደር የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዐለምአቀፍ ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ይስሐቅ ክፍሌ የወጣው ደብዳቤ የመለያየቱ ጊዜ ያበቃ ዘንድ ጥሪ አቅርቦዋል።
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በአንድ ፓትሪያርክ እና በአንድ እረኛ የምንመራ አንድ መንጋ መሆን እንችል ዘንድ ወጥነት ያለው ሰንሰለታዊ መዋቅር ባስቸክዋይ ተጠንቶ እንዲተገበርልን ልመናችንን እናቀርባለን” ሲል የምዕመናት አለም አቀፍ መህበር ጥሪ አቅርቦዋል።