በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ዕርቅን ለመፍጠር በሚካሄደው ውይይት ላይ ለመገኘት ከአዲስ አበባ የተወከሉት አባቶች አሜሪካ ገቡ

ህዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በውጭ የሚገኙ አባቶችና ከሐገር ቤት የመጡት ልዑካን በትናንትናው ዕለት ዳላስ ቴክሳስ ሲደርሱ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት እንዲያመጡ የተማፅኖ ፊርማዎ እየተሰበሰበ ይገኛል።

በውጭ የሚገኘው የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ መልከ ፀደቅ የሚመራው ልዑካን ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ከካናዳና አውሮፓ ትናንት ዳልስ ገብቷል።

ከብፁዕ አቡነ መልከፀደቅ በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ እንዲሁም ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በውጭ የሚገኘውን ሲኖዶስ መክረው ተገኝተዋል።

በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሚመራውና በኢትዮጲያ የሚገኘውን ሲኖዶስ የሚወክለው ልዑክ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ብፁዕ አቡነ አርናቴውስንና ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃን ያካተተ መሆኑን ለማወቅ ተችሎል::

ከዚህ ቀደሞ ከነበሩት ሁለት ውይይቶች በተለየ በሁለቱም ወገን አባቶች መካከል አብሮነት የታየበት ምዕመናኑም በከፍተኛ ደስታም ተስፋ በዳልስ የደብረምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ያደረጉበት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በዛሬው ዕለት የሚጀመረው ውይይት እስከ ፊታችን እሁድ ሕዳር 30/2005 የሚቀጥል ሲሆን የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና አባቶች ውጤቱን በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቁት መሆኑን የደረሱን አስተያየቶች ያስረዳሉ።