ህዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከመሬት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የከተማው ነዋሪዎች ያሰሙትን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ በቅርቡ ከንቲባውን አቶ መገርሳ ገለታን ጨምሮ 5 የካቢኔ አባላትን ከስልጣን ያወረደው መንግስት፣ ከአካባቢው ህዝብ ያልተመረጠ አዲስ ከንቲባ በመሾም ለህዝቡ ለማስተዋወቅ የጠራው ስብስባ በተቃውሞ እንዲበተን ተደርጓል።
ህዳር 21 ቀን 2005 ዓም ከፍተኛ የኦህዴድ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ቀነአ ኩማ የለገጣፎ ለገዳዲን ህዝብ በመሰብሰብ አዲስ ተሾመው የመጡትን አቶ አለማየሁ ውለታን ለማስተዋወቅ ሲሞክሩ፣ ህዝቡ ” ከንቲባ የሚመረጠው ከምክር ቤት ነው፣ ምክር ቤቱን የመረጥነው ደግሞ እኛ ነን፣ እናንተ ያመጣችሁልን ከንቲባ እኛ ያልመረጥነው ነው፤ ባልመረጥነው መሪ አንደራደርም ፣ ባልመረጥነው መሪም አንመራም።” በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት አዲሶቹን ተሿሚዎች አንቀበልም ካላችሁ ከጀርባችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ ማለት ነው፣ ብትቀበሉ ይሻላችሁዋል በማለት ለማስፈራራት ቢሞክሩም ህዝቡ ግን አሻፈረኝ ብሎአል።
ህዝቡን ይበልጥ ያስቆጣው ደግሞ ሌላው በሙስና ተገምግመው የወረዱት ምክትል ከንቲባው ተመልሰው ወደ ቦታቸው እንዲቀመጡ መደረጉ ነው። የፍትህ ሚ/ር ፣ ሚ/ር ዲኤታ የሆኑት አቶ ብርሀኑ ጸጋየ የቀድሞው ከንቲባና ባልደረቦቹ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ በግለሰቦቹ ላይ እስከአሁን ምንም አይነት ክስ አለመቅረቡም ነዋሪውን አበሳጭቷል።
በከተማው ነዋሪና በመንግስት መካካል ያለው ውዝግብ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ከአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ምስራቅ በኩል 21 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የለገጣፎ/ለገዳዲ ከተማ በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ልዩ ዞን ሥር በከተማ አስተዳደርነት እንድትመሰረት መደረጉ ይታወሳል፡፡በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ 2ሺ431 ሄክታር የመሬት ስፋት ያላት ሲሆን የተዋቀረችውም በሁለት ቀበሌዎች ነው፡፡የከተማው ማዘጋጃ ቤት ባሳተመው ብሮሸር የህዝብ ብዛቷ ከ18 ሺ እንደሚበልጥ ቢገልጽም የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ቁጥሩ ከአምስት ሺ እንደማይበልጥ መናገራቸውን ሰመጉ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መጥቀሱ ይታወሳል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ከሕዝቡ ቁጥር በላቀ መልኩ ወደሃያ ሺ የሚጠጋ ካርታ በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ከሌላ አካባቢ ለመጡ ሰዎች መሰጠቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በቅሬታ መልክ እንደሚያኑሱም በመግለጫው መጠቀሱ ይታወሳል።