የመለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የስልጣን ብወዛ መቀጠሉ ተዘገበ

ህዳር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዚህም መሰረት የአዳማ ከተማ ወይንም የናዝሪት ከተማ ከንቲባ ተነስተው በምትካቸው ሌላ ሰው መሾሙን ጉለሌ ፖስት የተባለው ድረ ገጽ ዘግቧል።

እርምጃው የኦህዴድን መካከለኛ አመራር የመጥረግ አካል እንደሆነም ተመልክቷል።

ከሩብ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት አዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጉታ ላንቼሮ በድንገት ተነስተው በምትካቻቸው የኳሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ባካር ሻሊ እንደተኰቸውም ተመልክቷል።

ባለፉት ሶስት ወራት በሙስናና በአስተዳደር በደል ተወንጅለው 35 የዞንና የወረዳ ባለስልጣናት ከሀላፊነታቸው መባረራቸውን፤ ከነዚህ ውስጥ አስራ አንዱ የተባረሩት ከቦረና ዞን እንደኋነም በዘገባው ተመልክቷል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ነጌሶ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰኢድ ጁንዲ በቅርብ ግዚያት ውስጥ ከስልጣን ከተባረሩ የክልሉ ሀላፊዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ከኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መባረራቸው የሚታወቅ ሲሆን ባለቤታቸውም በአሸባሪነት ተከሰው መታሰራቸው ይታወቃል።