ህዳር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ መኪና በመገጣጠም የመጀመሪያው በመኋን ሲሰራ የቆየው ሆላንድ ካር በኪሳራ ለመዘጋት የበቃው በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ባለመገኘቱ መሆኑን የኩባንያውን ባለቤት የጠቀሱ ዘገባዎች አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው ሳምንታዊው የቢዝነስ ጋዜጣ ካፒታል እንደዘገበው ለኩባንያው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።
የኋላንድ ካር ባለድርሻና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ለካፒታል ጋዜጣ ከአምስተርዳም በሰጡት ቃለምልልስ በኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም በአንድ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በመውደቁ አስቀድመው ውል የገቡላቸውን መኪኖች በኪሳራ ገጣጥመው ለመሸጥ መገደዳቸውን አስረድተዋል።
በእዚህም በእያንዳንዱ አባይ መኪና ላይ ተጨማሪ 80 ሺህ ብር ከኪሱ እያወጣ ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ መገደዱን፤ በአዋሽ መኪኖች ላይ ደግሞ ወጪው እስከ ሰላሳ ሺህ መድረሱን ዘርዝረዋል።
በብረ አቅም መድከም ሳቢያ የተከተለውን ይህንን ችግር ለመሻገር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ጠይቀው እንዳልተሳካላቸው ፤ ከቻይና የጠየቁት ብድር ደግሞ በመዘግየቱ ኩባንያው ለመክሰር መገደዱን አብራርተዋል።
ኩባንያው የገጠመውን ችግር ለመፍታት እንዲሁም በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር በመነጋገር የጀመረው የአቶቡስ ግንባታ ፕሮጀክት ብዙ ርቀት ከሄደ በሆላ መስተዳድሩ ውሉን በማፍረሱ የኩባንያው ኪሳራ የከፋ እንዲሆን እንዳደረገውም በዘገባው ተመልክቶል። አሀዱ የሚባል አውቷቡስ አምረተው እንደነበርም አስታውሰዋል።