የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽነር ከእስር ተለቀቁ

ህዳር ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከወራት በፊት በጋምቤላ በተገደሉትን 19 ተማሪዎች እና በሳውዲ ስታር ሰራተኞች ላይ በተፈጸመ ጥቃት እጃቸው አለበት ተብሎ ለወራት በእስር ላይ የነበሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ግለሰብ ከእስር ተለቀዋል።

ኮሚሺነሩ ከእስር የተለቀቁበት ምክንያት ግልጽ አይደለም የሚለው የጋምቤላ ዘጋቢያችን በአሁኑ ጊዜ በመዘጋጃ ቤት ውስጥ ስራ ተሰጥቷቸው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጋምቤላ አሁንም ሙሉ በሙሉ ተረጋግቷል ብሎ መናገር እንደማይቻል ዘጋቢያችን ገልጿል።

ዜና 3

መኢአድ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲቆም ጠየቀ

ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ በክልሎች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሷል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ፣  በክልሎች የሚታየውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለማውገዝ የዘገዩት ፣ ድርጅታቸው መግለጫ ሲያወጣ ኢህአዴግ በክልሎች መግለጫ ሰጥታችሁዋል የሚላቸውን ዜጎች በተለይም አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትን እየመረጠ ስለሚገድል፣ ንብረት ስለሚቀማ እና ስለሚያስር ነው ብለዋል።

ጥቃቱ በተለይ በደቡብ በጉርዳ ፈርዳ ወረዳ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ የበረታ ሲሆን፣ አማራ መሆንና አማርኛ መናገር ወንጀል ሆኗል ብሎአል።

መኢአድ በመጪው አዲስ አበባና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ለመሳተፍ አለመወሰኑን ፣ ከ34 ፓርቲዎች ጋር ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡንም ገልጿል።

የገዢው ፓርቲ ጫና የጎላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞቱ በሁዋላ ነው የሚለው መኢአድ፣ ከዚህ ቀደም ሁሉንም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅልለው ይዘውት ስለነበር፣ አሁን እርሳቸው ከሞቱ በሁዋላ ኢህአዴግ ጠንካራ ሰው ለማግኘት ባለመቻሉ በፍርሀት ውስጥ ይገኛል ሲል ፓርቲው ግልጿል።
አማርኛ ተናጋሪውንና እና መኢአድን ፈርተውታል የሚለው ፓርቲው፣ አማርኛ ተናጋሪው ስልጣን ላይ ከወጣ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው ስለሚያከሽፍ መኢአድን ማዳከምና አማርኛ ተናጋሪውን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል መነጠልና መምታት ፈልገዋል በማለት በመግለጫው ላይ ማስታወቁን ዘጋቢያችን ገልጿል።

አሁን ኢትዮጵያን እየመሩት ያለው ኢህአዴግ ሳይሆን በጎጥ የተደራጀ ወታደራዊ ቡድን ነው ያሉት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር፣ እየሞትንም እየታሰርንም በሰላማዊ ትግል እንቀጥላለን ብለዋል።
ዜና