ህዳር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት “የአቶ መለስን ራዕይን ለማሳካት” በሚል መፈክር ለህዳሴ ግድብ ማሰሪያ የሁለተኛ ዙር መዋጮ የማሰባሰብ ዘመቻ በይፋ ጀምሯል፡፡
ባለፈው ዓመት ለግድቡ ማሰሪያ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች በዓመት የሚከፈል የአንድ ወር ደመወዝ
በስጦታ መልክ ቢለግሱም ገዥው ፓርቲ ቁጠባን ለማበረታት በሚል ስጦታው ወደ ቦንድ ግዥ እንዲቀየር በወሰነው መሰረት
ክፍያቸውን ላጠናቀቁ ተቋማትና ሰራተኞች የቦንድ ሰርተፊኬት በመስጠት ላይ ከመሆኑም ባሻገር ሰሞኑን
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ይፋዊ የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም በአዲስአበባ በሚሌኒየም
አዳራሽ አካሂዷል፡፡
ይህም በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ሰራተኛው እንዲያዋጣ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሎ
መገመቱንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰራተኞች፣የንግዱ ማኀበረሰብ አባላት፣ባለሃብቶችና ሌሎችም የኀብረተሰብ ክፍሎች ያዋጡት ገንዘብ
ተደማምሮ ዘጠኝ ቢሊየን ብር ገደማ መድረሱን ይህም ሆኖ ግን ከሰራተኞች በስተቀር በተለይ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች
የገቡትን ቃል ባለመፈጸማቸው ቃል ከተገባው መሰብሰብ የተቻለው ከአንድ ሶስተኛ በታች መሆኑ የገዥውን ፓርቲ
ከፍተኛ አመራሮች አስደንግጧል፡፡
ባለሃብቶቹ ገንዘቡን በወቅቱ ላለመልቀቃቸው ከሰጡት ምክንያቶች መካከል ከአንድ ዓመት በፊት የግድቡ ዕቅድ ይፋ በሆነበት ወቅት ቦንድ የሚገዙ ባለሃብቶች ሰርተፊኬቱን ለባንክ ብድር ማስያዣ ጭምር ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በመንግስት ቃል ከተገባ በኃላ በአፈጻጸም መደናቀፉ በርካታ ባለሃብቶችን ቅር በማሰኘቱ ነው፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ ሰራተኛው ሳይወድ በግዱ በቀጥታ ከደሞዙ ተቆርጦ ገንዘቡ ገቢ የሚሆን በመሆኑ፣ በትክክል
መሰብሰብ የቻለው የሰራተኛውን ክፍያ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰበሰበ፣ገንዘቡ በምን መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ በእነ አቶ በረከት
ስምኦን የሚመራው የህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ም/ቤት በየጊዜው ይፋ ከማድረግ መቆጠቡ ጥቂት የማይባሉ የመንግስት
ሰራተኞችን አሳስቧል፡፡
ሕዝቦ ጦሙን እያደረ ሳይተርፈው ገንዘብ እያዋጣ ዝም ማለት ከግልጽነትና ተጠያቂነት አንጻር አነጋጋሪ መሆኑን ያነጋገርናቸው ሰራተኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ም/ቤት ውስጥ የተሰገሰጉ የመንግስት ባለስልጣናት ብዙዎቹ በሙስናና ብልሹ አሰራር ስማቸው በክፉ የሚነሱ ግለሰቦች መሆናቸውም ጥርጣሬውን እንደሚያጎላው ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱ የመንግስት ሰራተኛው ተርፎት ሊያዋጣ ቀርቶ ቤተሰቡንም መመገብ የማይችልበት ደረጃ መድረሱ የዘንድሮን መዋጮ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ምንጫችን ገልጿል፡፡
ኢሳት ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ የግድቡ ሰራተኞች ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡