በደራ ወረዳ በአንዲት ሴት ላይ የተፈጸመውን ግፍ በይፋ ያጋለጡት የቀበሌው ሊቀመንበር ቃለምልልስ ሰጡ

ህዳር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ በገብሮ ቀበሌ የወረዳው የአስተዳደርና ፍትህ ሀላፊ የቅርብ ዘመድ የሆነ አቶ አየለ የተባለ ከሌሎች ሁለት ግብረ አበር ፖሊሶች ጋር በመሆን በቀበሌው የሚኖርን አንድን ግለሰብ መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ሰበብ ግለሰቡንና ባለቤታቸውን ልብሳቸውን በማስወለቅ እርቃናቸውን እንዲታሰሩ ማድረጉን፣ እንዲሁም ባልየው ብልቱ በገመድ እንዲታሰር ከተደረገ በሁዋላ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ እርቃኑዋን የሆነቸው ባለቤቱ ብልቱን በገመድ እንድትስብ እንዲሁም ብልቱን እንድትስም ማስደረጉን እንዲሁም  የመንግስት ሹሙ ግለሰቡዋን በእርግጫ በመምታቱ የስድስት ወር ልጅ እንድታስወርድ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

 

ይህን ግፍ ይፋ ያደረጉት የገብሮ ቀበሌ ሊቀመንበር የሆኑት ቄስ ጣሴ ንጉሴ ሲሆኑ ፣ ሊቀመንበሩ እንዳሉት ለመንግስት ስራ ወደ ቀበሌያቸው የተላከው ሹም እርሳቸውን ሳያማክርና ከእርሳቸው ጋር ሳይተባበር ወደ አርሶ አደሩ ቤት ማምራቱን ገልጸዋል።

 

እርሳቸው በቦታው እንዳልነበሩ የተናገሩት ሊቀመንበሩ ይሁን እንጅ ድርጊቱ መፈጸሙን የአካባቢው ሰዎች በመናገራቸው፣ ከወረዳ፣ ከቀበሌና  ባለስልጣናት ጋር በመሄድ ለማጣራት መቻላቸውንና ድርጊቱም እንደተፈጸመ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

 

አርሶ አደሩ ሞዴል ገብሬ ነበር የሚሉት ቄስ ጣሴ፣ የወረዳው የጸጥታና አስተዳዳር ሹሙ ግለሰቡን ለቤት መጠበቂያ የሚጠቀምበትን የጦር መሳሪያ እንዲያመጣ በጠየቀው ጊዜ አርሶደሩም መሳሪያ እንደሌለው፣ መግለጹን አውስተዋል። የወረዳው ሹምም ወደ ውስጥ በመግባት የአርሶአደሩን መሳሪያ ፈልጎ ካገኘ በሁዋላ፣ በመሳሪያው አርሶ አደሩን ጀርባውን ሲመታው፣ የመሳሪያው ሰደፍ መሰበሩን ገልጸዋል።

አብራው የነበረችውን ሚስቱንም ልብሷን ከፍ አድረጋ እንድትይዝና እራቁቷን ሆና እንድትታይ አስደርጓታል።  እንዲሁም ጌታው ባልሰው በመባል የሚጠራውን የልጃቸውን ብልት በአጎበር ገመድ በማሰር ና ሚስቱም ሌሎች አስጸያፊ ድርጊቶችን እንድትፈጽም ማድረጉን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። እንዲሁም ወጣቱዋን በሰደፍ ሲመታት የስድስት ወር ልጇን አስወርዳለች።

 

ቄስ ጣሴ አክለውም ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች አዝመራ በጎረበቶችና በአካባቢው ሰዎች እንዲሰበሰብ መደረጉንና ግለሰቦችን ለማረጋጋት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ። ባልየውና ልጁ ከህመማቸው እያገገሙ መሆኑን፣ ሚስትየዋ አሁንም በአካባቢው ባለ ጤና ጣቢያ ህክምና ላይ መሆኑዋን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

 

ከእንግዲህ ወዲያ እንዲህ አይነት የመንግስት ሹም ወደ ቀበሌያቸው እንዳይላክባቸው ለከፍተኛ አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። ቄስ ጣሴ ይህን ግፍ በድፍረት ይፋ ያደረጉት ከዞን፣ ከወረዳ እንዲሁም ከቀበሌ የተውጣጡ አመራሮች ለ4 ቀናት ባካሂዱት ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው ላይ  በድርጊቱ የተበሳጨውን የአካባቢውን ህዝብ ለማረጋጋት በስብሰባው የተሳተፉት  “ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ እንዲህ አይነት ድርጊት እንዲፈጽም ከመንግስት ታዞ አለመሆኑንና በግል ተነሳስቶ መሆኑን” እንዲያስረዱ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል። መንግስትም በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

 

ይህ ግለሰብ ባሂት በሚባለው ቀበሌ ደግሞ አንድን ግለሰብ በችቦ ማቃጣሉን አንድን የምክር ቤት አባል ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፤፡

የወረዳው የፍትህና አስተዳዳር ሀላፊ ከድርጊቱ ጀርባ እጁ እንዳለበትም ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

 

ግለሰቡ  በማዳበሪያ እና በሌሎችም ምክንያቶች እያሳበበ አባዎራዎችን ወደ እስር ቤት በመወርወር  እርሱና ጓደኞቹ ሚስቶቻቸውን እንደሚደፍሩም ታውቋል።

 

ግለሰቡ ቀደም ብሎ በሰራው ወንጀል ተከሶ የነበረ ቢሆንም፣ ያለምንም ቅጣት ተለቆ በሀላፊነቱ ላይ እንዲቆይ ተደርጓል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መስፍን ታየ ድርጊቱ መፈጸሙን አምነው ፣ የሚሊሺያ ዘርፍ ሀላፊው በህግ ስር ውሎ ጉዳዩ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።