ፓትሪያርክ መርቆሬዎስ ከነሙሉ ስልጣናቸው ወደመንበራቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ለኢሳት እንደተናገሩት፤ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ከነሙሉ ስልጣናቸው ወደመንበረ-ፓትሪያርኩ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቅዱስ ፓትሪያርኩ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የሚገልጽ ደብዳቤ ለአቃቤ መንበረ ፓትሪያርኩ፤ ለአቡነ ናትናኤል መጻፋቸውንና ደብዳቤውም በሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ መነበቡን በተለይ ለኢሳት ገልጸዋል። በሀገር ቤትና በስደት በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ስምምነት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ለማድረግ በውጭ የሚገኙት አባቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ ገለጸዋል። በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል አራት የመደራደሪያ ነጥቦች መኖራቸወንና “የብጹእነታቸው ወደመንበራቸው መመለስ ዋንኛ የመደራደሪያ ነጥብ መሆኑን” ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ጨምረው አስታውቀዋል። ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ በአዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖዶስ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ለመምረጥ የሚያስችለውን ዝግጅት መጀመሩን የሚጠቁም መግለጫ መውጣቱን የተመለከቱ መሆኑን አስታውሰው፤ በጉዳዩ ላይ ከሸምጋዩ ኮሚቴ ጋር መነጋገራቸወንና ነገሩ ያበቃለት አለመሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር ታምራት ላይኔ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ከስልጣናቸው እንዲነሱና እንዲሰደዱ ባሳደሩት ተጽእኖ መጸጸታቸውን ብጹእነታውን ይቅርታ ለመጠየቅ እንደሚፈልጉም እንደገለጹላቸው፤ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ አረጋግጠዋል።