፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዜሮ አንድ ከ 2000 በላይ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ።
የክፍለ ከተማው ፖሊሶች በነቂስ ወተው ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶች የፈረሱበትን ዘመቻ ነዋሪውን በማሰርና በመደብደብ ጭምር አስፈጽመዋል።
በተለምዶ ሀና ማሪያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዛሬ ጥዋት ሶስት ግሬደር ተሰማርቶ ባደረገው የማፍረስ ዘመቻ መስኪድና ቤተክርስትያን ጭምር ፈሮሶል ተብሎል። ኢሳት ሬድዮ ያናገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በአሁኑ ሰአት የ2000 አባወራ ቤተሰብ ሜዳላይ ወድቆ ይገኛል፣ ህጻናትና አዛውንት ለብርድና ለቸነፈር ተጋልጠዋል ብለዋል።
ከሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ የተሰሩ ቤቶች በዛሬው ዘመቻ ፈርሰዋል ያሉት ነዋሪዎች ንብረትና እቃቸውን እንኮን የማውጣት እድል ሳይሰጣቸው የማፍረሱ ስራ ዛሬ ጥዋት በድንገት መፈጸሙ እነዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ በእድሜ በኖርኩበት 47 አመት መኖሬን የጠላሁበትና ማንነቴን የጠየኩበት ግዜ ዛሬ ነው ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
መንግስት የአባትነት ሚናነው ያለው እኒህ ነዋሪ መሰረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎት የማሞላት ሚናውን ከመጫወት ይልቅ ክ 10 000 ያላነሱ ሰዎችን ቤታቸውን አፍርሶ ለጎዳና መዳረግ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ብለዋል፡፤
ሌላው ነዋሬ ደግሞ ፖሊሶቹንና የወረዳ ሀላፌዎችን ነዋሪው እያነባ የሁለት የሶስት ቀን ግዜ ይሰጠን ሌላው ቢቀር ማረፊያ እንፈልግ እቃችንን እናውጣ ብለው ሲለምኑ አንዱ ፖሊስ የኢትዮጵያ ህዝብ ጎዳና ነው የሚኖረው እናንተም ጎዳና ለትኖሩ ትችላላችሁ ሲል መዘባበቱን ገልጠው በምላሹ ማዘናቸውንና በመንግስት ሰዎች ተስፋ መቁረጣቸውን ተናግረዋል።
ያነጋገርናቸው የወረዳው የመሬት አስተዳደር ባለሙያ በከተማ ቦታ ካርታ ላይ ያልሰፈሩትን ነዋሪዎች ቤት ነው ላፕ ቶፓችንንና ጂፒ ኤስ በመጠቀም ያፈረስነው ብለዋል።