ጥቅምት ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአካባቢና የአዲስአበባ ከተማ ምርጫ ተቃዋሚዎች እስካሁን ምንም ዓይነት
ዝግጅት አለማድረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡
ምርጫ ቦርድ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ምርጫው የሚያካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገ
ሲሆን በዚህ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫው ዕጩዎቻቸውን ለማስመዝገብ የቀራቸው ጊዜ ሶስት ወራት
ብቻ ነው፡፡
ይህም ሆኖ እስካሁን አንድም ፓርቲ በምርጫው እንደሚሳተፍ የገለጸበት ሁኔታ ካለመኖሩም በላይ ምርጫ
ስለመኖሩም እየተነገረ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ኢህአዴግ ሆን ብሎ ስለምርጫው ብዙም ሳይወራ በግርግር አሸናፊ ተብሎ
እንዲያልፍ እንደሚፈልግ ምንጫችን አስታውሶ ተቃዋሚዎች ግን በአዲስአበባ እንኳን ጥቂትም ቢሆን ወንበር ለማግኘት
ከወዲሁ መስራት አለመቻላቸው በጣም መዳከማቸውን እንደሚያሳይ ገልጾአል፡፡ትልቁን ተቃዋሚ ፓርቲ መድረክን ጨምሮ
እንደ መኢአድ ያሉ ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ እስካሁን አለመወሰናቸው ታውቋል፡፡ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው የዜና ምንጫችን ጠቁሟል፡፡
አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ከምርጫው በፊት በአገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ችግሮች ጋር በተያያዘ ለመወያየት ፍላጎት እንዳላቸው
ከሳምንት በፊት በአዳማ ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ ያሳወቁ ቢሆንም በምርጫ ቦርድ በኩል ያለው ዝምታ ግን
ጊዜ መግደያ መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ፓርቲዎቹ ለመወያየት ያቀረቡት ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ለምርጫው እየተዘጋጁ ቢጠባበቁ የተሻለ ዕድል እንደሚኖራቸው ምንጫችን መክሮአል፡፡ይህ ካልሆነ ግን ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካሪ ም/ቤት በሚል በየዓመቱ በጀት የሚቆርጥላቸውን ፓርቲዎች በመያዝ እንደተለመደው 99 በመቶ አሸነፍኩ ብሎ እንደሚያውጅ ከወዲሁ የተረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ከአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ አቶ አስራት ጣሴ ጋር ቃለምልልስ አድርገናል
በደቡብ የክልል የም/ቤትና የቀበሌ ምርጫዎችን ጨምሮ በአዲስአበባ የከተማ አስተዳደር፣የዞንና የወረዳ ም/ቤቶች
ምርጫ በሚያዚያ ወር 2005 ለማካሄድ ቦርዱ አቅዶአል፡፡