ለአማራው መብት የሚታገል ሲቪክ ተቆም ተመሰረተ

ባለፉት 21 አመታት በአማራው ብሄረሰብ ላይ በገዥው ፓርቲ የደረሰበትን መፈናቀል፣ መገፋት መገለልና የዘር ማጽዳት እርምጃ ለመታደግና ለመታገል ያለመ ሲቪክ ድርጅት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ተመሰረተ::
ሞረሽ ወገኔ የአማራው ድርጅት የተሰኘው ይህ ሲቪክ ተቆም ከትላንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላለፉት 21 አመታት የአማራው ብሄረሰብ አባል ተዋራጅና ተሸማቃቂ ተደርጎል፣የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅሞቹ ተነጥቀዋል ከምስራቅ፣ከደቡብ ምእራብ፣ከደቡብና ከመሀል ኢትዮጵያ መኖር አትችልም ተብሎ ሀብት ንብረቱ ተነጥቆ ተባሮል ሲል ገለጧል::
ላለፉት 21 አመታት በገዥው ፓርቲ በአማራው ህብረተሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ ሊገታ ይገባዋል ያሉት የሞረሽ ወገኔ ሊቀመንበር አቶ ተክሌ የሻው ይህን ለማድረግ መደራጀት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ሆኖብናል ብለዋል::
ግባችን የአማራው ህልውና እንዲጠበቅና በመላው ሀገሪቱ የመስራትና የመኖር መብቱ እንዲከበር ነው ያለው የሞረሽ ወገኔ የአማራው ድርጅት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህን ሲያደርግ የገዥው ፓርቲን የአንድ ብሄረሰብን የማግነን፣ የከፋፍለህ ግዛ መርህንና ዘረኝነትን አጥብቆ በመታገል እንደሆነ ገልጧል::
አማራው ሲደራጅ አምርሮ የሚታገለው ግፍ ያደረሰበትን የገዥው ፓርቲን ስርአትና የቀረጸውን ፖሊሲ ነው ያለው የሞረሽ ሊቀመንበር አቶ ተክሌ የሻው ማህበረሰባችንን የማዳን እንጂ ሌላውን የማጥቃት አላማ የለንም ብለዋል::
የድርጅቱ መስራቾችና አባላት አማራው ከሚደርስበት ግፍና በደል ለማውጣትና በሺዎች ለሚቆጠሩ ለተፈናቀሉ ወገኖቹን ለመታደግ እውቀታቸውን ፣ ገንዘባቸውንና ሀሳባቸውን አስተባብረው ለመስራት መቁረጣቸውን ባወጡት የአቆም መግለጫ አስታውቀዋል::