ጥቅምት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች መንግስት ከገቢያቸው ጋር ያልተጣጣመ ታክስ እንዲከፍሉ በማስገደዱ ድርጅታቸውን ለመዝጋት እየተገደዱ መሆኑን ለኢሳት ገልጠዋል።
በደቡብ ጎንደር ወረታ ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ነጋዴ እንዳለው በግብር የተነሳ ህዝቡ እየተሰደደ ነው ብሎአል ።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ በጨርቃጨርቅ ስራ ላይ የተሰማራ ነጋዴ በበኩሉ በግብር የተነሳ ቤተሰቡን እስከመበተን መድረሱን ተናግሯል ወረታ በእህል ንግድ ላይ የተሰማራ ነጋዴ በበኩሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ ማደር እንደ ሀጢያት እየተቆጠረ ነው ብሎአል።
ነጋዴዎቹ ለመንግስት ባለስልጣናት አቤት ቢሉም በቂ ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል
የዞኑ የገቢዎች ሀላፊ የሆኑት አቶ አባቡ በነጋዴዎች የቀረበውን ቅሬታ አይቀበሉትም። ነጋዴዎች ግብር በዛብን ካሉ ይግባኝ ማለት እንደሚችሉና ጉዳያቸውን በይግባኝ ሰሚ እንደሚታይላቸው ገልጸዋል::