የእስራዔል መንግስት 237 “ፈላሻ ሙራዎችን” ከኢትዮጵያ መውሰዱን አስታወቀ

ጥቅምት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “የእርግብ ክንፍ” የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚሁ ዘመቻ ከተጓጓዙት ፈላሻ ሙራዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ሕፃናት ሲሆኑ፣ እስከ ሕዳር 2006 ዓ.ም ድረስ ተጨማሪ 2000 ቤተ እስራኤላውያንን ከጎንደር ለመውሰድ እቅድ እንደያዘ የ የእስራኤል መንግስት ይፋ አድርጓል።፣

ለነኚሁ ተጓዦቹ ማረፊያ ይሆን ዘንድም፣ አስፈላጊው ነገር የተሟላለት 16 የመጠለያ ጣቢያ ነጂቭ በረሃ ላይ መዘጋጀቱ ታውቋል።

በእስራኤል ከሚኖሩት ፈላሻ ሙራዎች መካከል 80 ሺህ ያህሉ የተወለዱት ኢትዪጵያ ውስጥ ሲሆን፣ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ብቻ 120 ሺህ ፈላሻ ሙራዎች ከኢትዮጵያ ወደ እስራዔል ተጓጉዘዋል። ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው ሃይማኖታቸውን ወደ ይሁዲ እንዲቀይሩ ተደርገዋል። በዚሁ መሰረት አሁን የተጓጓዙትም ቤተ እስራኤላውያንም ከምንም ነገር በፊት በዚሁ መንገድ ማለፍ ይኖርባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የእስራዔል መንግስት፤ ወይዘሮ በላይነሽ ዝቫዲያ የተሰኙ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱ ቤተ እስራኤላዊ፣ በኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርጎ ባለፈው ዓመት መሾሙን ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።