ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ፤ህግ ሊዘጋጅ ነው

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ይህ የተጠቆመው፤   የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ  ላይ ነው።

እንደ ስብሰባው ምንጮች ገለፃ ምልአተ ጉባኤው በጥቅምት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ውሎው በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅት ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በውሳኔው መሠረት ቀደም ሲል የሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማሻሻያ እንዲሠራ የተሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ምሁራን ኮሚቴ፤ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅንም አዘጋጅቶ በኅዳር ወር መጨረሻ ያቀርባል፡፡

ከዚያም በተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ እና በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ተወያይቶ ሕግጋቱን የሚያጸድቅ ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ  በመጪው ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም  እንዲጠራ መወሰኑን የጉባኤውን ተሳታፊዎች  ጠቅሶ ደጀ-ሰላም ዘግቧል።

በእስልምና እምነት የመጂሊስ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳበት የኢህአዴግ መንግስት፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን  በምታካሂደው በስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዙሪያ  እጁን ለማስገባት  ፍላጎት ከማሳየት አልፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ሲዘገብ ቆይቷል።

በፓትርያርኩ ምርጫ ዙሪያ ኢህአዴግ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ፤በአገር ቤትና በውጪ ያለውን ሲኖዶስ በማስታረቅ ቤተክርስቲያንን ወደ አንድ ለማምጣት እየተካሄደ ያለውንና ወደ መፍትሔ ጫፍ እየደረሰ ነው የተባለውንየ እርቀ-ሰላም ሂደት  ያጨናግፈዋለወ ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በመሆኑም መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚል አንቀጽ በህገ መንግስቱ ያካተተው መንግስት፣ ለቤተ-ክርስቲያኒቱ ሰላም ሲል እየታማበት ካለው እውነታ እጁን እንዲሰበስብና የቤተ-ክርስቲያንን ጉዳይ ለቤተ-ክርስቲያን እንዲተው  እነዚሁ ወገኖች አሣስበዋል።