ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መንግስት የሚናገረው 11 ከመቶ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በምን ስሌት እንደመጣ ልንረዳ አልቻልንም፤ ምናልባት ችግሩ የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን አቅም ማነስ ሊሆን ይችላል ሲሉ፤ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ ከአዲስ ፎርቹን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የአይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ የሚያወጣቸው ቁጥሮች ተመሳሳይ ቢሆኑም፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው የ11 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት ግን ከኛ ቁጥሮች ጋር ፈጽሞ አይገናኙም ሲሉ ተናግረዋል።
ልዩነቱ ከምን እንደሚመነጭ ለማወቅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ጉዋንግ ቼን፤ ችግሩ የመነጨው ከማእለከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን ብቃት ማነስ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት፤ የባለስልጣኑን ብቃት በማሻሻል ስራ ላይ የሚውል፤ 10 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ አብይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ቃለምልልስ የሰጡት የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር፤ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ከብሄራዊ ባንክ እንደማይበደር ቃል ቢገባም፤ አሁንም ከፍተኛ የሆነ የአቅምና የእቅድ አለመመጣጠን ስላለ፤ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ሳይበረድ ወይንም ገንዘብ ሳያትም በምን መልኩ እቅዱን እንደሚያሟላ አልታወቀም ብለዋል።
መንግስት ብር ካተመ ወይንም ከብሄራዊ ባንክ ከተበደረ፤ የዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ያሉት ዳይሬክተር፤ በአገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ሁኔታ ከሌለ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ ይቸግረናል ብለዋል።
የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (ኤይ ኤም ኤፍ) ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ባወጣው ሪፖርት፣ ከዚህ ቀደም መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ያገኘው የነበረውን ብድር በማቆሙ፤ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለማውረድ ቢረዳውም፣ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ግን መንግስት ከብሄራዊ ባንክ መበደሩን ለመቀጠል ዕቅድ መያዙ የዋጋ ግሽበቱን እንደሚያንረው አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን ቀደም ሲል በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግሥታቸው ከብሔራዊ ባንክ እንደማይበደር ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከብሄራዊ ባንክ አንበደርም ቢሉም፤ አይኤምኤፍ ግን በሪፖርቱ መንግሥት በዚህ የበጀት ዓመትም የመበደር ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።
የአለም ባንክ ዳይሬክተርም ምንግስት ከብሄራዊ ባንክ ካልተበደረ፤ ያቀዳቸውን እቅዶች ከየት አምጥቶ እንደሚሞላ ፍንጨ የለንም ሲሉ ከአዲስ ፎርቹን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
በተያያ ዜና በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ የተጠየቁት የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ግዜ ይፈልጋል ብለዋል።
ባንኩ የኢትዮጵያ መንግስት ስለሚከተለውንና ዴሞክራሲን ያቀጭጫል የሚባለውን ልማት-መር የኢኮኖሚ ስርአት (ዴቭሎፕመንታል ስቴት) ይደግፋል ወይ ተብለው የተጠየቁት የባንኩ ዳይሬክተር፤ እሱ የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳይ ነው ሲሉ መልሰዋል።