የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ስብሰባ ቀጥሏል፤ አዲስ አበባ በአራት አገረ-ስብከቶች ትከፈላለች

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደቀጠለ ሲሆን፤ ሲኖዶሱ በከፍተኛ ሙስና፤ በመልካም አስተዳደር እጦትና በጎሰኝነት የሚታመሰው የአዲስ አበባ አገረስብከት በአራት አገረ ስብከቶች እንዲከፈል መወሰኑ ታውቋል።

በአመት ሁለት ግዜ የሚደረገው የሲኖዱ ስብሰባ፤ ባለፈው ሰኞ የተጀመረው የጥቅምቱ ስብሰባ፤ በእስካሁኑ ውሎው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን፤ የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ጉዳይና ከስራ ቅልጥፍና ጋር በተያያዙና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መምከሩ ታውቋል።

ሲኖዶሱ፤ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ተብሎ በአራቱ ማእዝናት ተከፍሎ በአዲስ አበባ የሚገኙት 160 አድባራትና ገዳማት ለአራት እንዲከፈሉ መወሰኑን ደጀሰላም የተሰኘው ድረገጽ ዘግቧል።  አገረ ስብከቶቹ በመጪው ግንቦት ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚሾሙላቸው ለስብሰባው ቅርበት ያላቸው የደጀሰላም ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በውጭ ከሚገኘው ሲኖዶስ ጋር ስለሚደረገው እርቅ ሰላም ሁኔታ፤ ከኅዳር 26 እስከ ህዳር 30 ቀን በአሜሪካ ለሚቀጥለው የእርቅ ድርድር፤ ሲኖዶሱ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስንና ብፁዕ አቡነ ገሪማን በልኡክነት፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን ደግሞ በጸሐፊነት እንደመደበ ታውቋል።

በሌላ ዜና፤ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ አቡነ ናትናኤል የተመራ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ቡድን ትናንት ሀሙስ ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፤ አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋራ ባለፈው መንግስት በተወረሱትና በአሁኑ ሰዓት በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚተዳደሩት የተለያዩ የቁጠባ እና ቪላ ቤቶች፣ አፓርትመንቶች፣ ሕንጻዎችና መጋዘኖች መመለስ ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።

ብዛታቸው 283 የሚደርሱ  በአራት ኪሎ መንበረ ፓትርያርክ አጠገብ የሚገኙት መንትያ ሕንጻዎች፣ በተወካዮች ም/ቤት፣ በፌዴሬሽን ም/ቤት፣ በኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ በፊኒፊኔ /ዱክ/ ሆቴል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጄንሲ የሚተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ብዛታቸው፤ እንዲመለሱላት ያለበለዚአም መንግስት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ኪራይ እንዲከፍል ጥያቄዎች ማቅረባቸው ታውቋል።

በአቶ ኩማ በኩል የተሰጠው ምላሽ አልታወቀም።