የሙስሊም አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ዛሬ ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው ያለ አንዳች ውሳኔ ለሰኞ ቀጠሮው መዛወሩ ተገለጠ።ምንጮቻችን ከአዲስ አበባ እንደዘገቡት የአመራሮቹ የፍርድ ሂደት ቀድሞ የሚታየው በአራዳ ፍርድ ቤት የነበረ ቢሆንም ዛሬ የቀረቡት ግን በልደታ ፍ/ቤት ነው ።

የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት በተከሰሱበት የሽብርተኝነት ወንጀል ለብይን ቀጠሮ የተሰጣቸው ትላንት የነበረ ቢሆንም ያላ አንዳች የቀጠሮ ለውጥ ዛሬ እንዲቀርቡ መደረጉና የትላንቱ የመሰረዙ ምክንያት አልታወቀም ሲሉ ምንጮቻችን ከአዲስ አበባ ዘግበዋል ።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ በእስር ቤት ያሉት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራሮቹ በመንግስት ተወስዶባቸው የነበረ ላፕቶፓቸው በሳምንቱ ውስጥ ስለተመለሰላቸው ነገ በሚከበረው የሙስሊሙ የኢድአላድሀ በአል ይፈታሉ የሚል እምነት አሳድሮ እንደነበርም ይኸው የምንጨቻችን ዘገባ የስረዳል ።