ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-“የቀጣዩ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ከእርቅ እና ከአንድነት በኋላ እንጂ በችኮላ መሆን እንደሌለበት አጽንዖት እየተሰጠው ባለው በአሁኑ ወቅት; የየራሳቸውን ወገን “ፓትርያርክ” አድርገው ለማስሾም ፍላጎት ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች፣ በይፋ ብቅ ማለት መጀመራቸውን በዝርዝር የዘገበው ደጀ-ሰላም ነው።
እንደ ደጀ ሰላም ዘገባ፤ ቀጣዩን የፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ በቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ በስፋት እጁን ያስገባው መንግስት ነው።
የሙስሊሙ ህብረተሰብ የራሱን የመጂሊስ አመራሮች በራሱ ፍላጎት እንዳይመርጥ <ጣልቃ ገብቷል>ተብሎ እየተወቀሰ የሚገኘው እና ላለፉት አስር ወራት ከሙስሊሞች ተከታታይ ተቃውሞዎች እየተሰነዘሩበት ያለው የኢትዮጵያ መንግስት፤ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም ውስጥ ሊደረግ በታሰበው የፓትርያርክ ምርጫ እጁን አስገብቷል መባሉ፤ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
ድረ-ገጹ እንዳለው፤የአራተኛውን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፍላጎት፤ መንግስት ‘በራሱ መንገድ አረጋግጧል።’
ይሁንና፤መንግስት ቅዱስነታቸው ወደ አገር ቤት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት በአዎንታዊነት ተቀብሎ ሲያበቃ፤ የእርሳቸው ፍላጎት ምንም ይኹን በፓትርያርክነት መንበሩ ተቀምጠው ማየት እንደማይሻ ፤እንዲሁም <ተጀምሯል> የተባለው ዕርቀ ሰላም የፓትርያርክነት ሹመትን ሳይጨምር ሊፈጸም እንደሚችል አቋም እንደያዘ ተገልጿል።
የአቡነ መርቆርዮስን በፕትርክና መቀመጥ አጥብቆ የተቃወመው መንግስት ፤ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩን ወይም ስድስተኛውን የፓትርያርክ ምርጫ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅት- ቀን ቆርጣ በፍጥነት እንድታከናወን እንደሚሻ ነው የተነገረው፡፡
በዚህም መሰረት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በቀዳሚነት፤ የእርሳቸው ካልተሳካ ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በአማራጭነት ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ፤ የመንግስት ፍላጎት እንደሆነ ተዘግቧል።
በሌላ በኩል በአንድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለስልጣን የሚመራ፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አለቆችንና ጸሐፊዎችን በአባልነት የያዘና በቅጽል ስሙ <ቡድን ስምንት>ተብሎ የሚጠራ አካል፤ በአዲስ አበባና በደብረ-ዘይት በሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች እየተሰበሰበ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ የምክክር ስብሰባዎችን እያካሄደ ይገኛል።
በሊቀ-ሊቃውንት እዝራ ተክለጊዮርጊስ እየተመራ ነው በተባለው በዚህ ስብሰባ ፤ብጹዕ አቡነ ማትያስ ቀዳሚው የፕትርክና ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ተሰምቷል።
በቤተ-ክህነት አስተዳደር ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ ሌሎች የኢህአዴግ አባላት ደግሞ፤ <<ፕትርክናው በብሔረሰብ አለያም በክፍለ-ሀገር ተዋጽኦ ታይቶ ፤ላልደረሰው ብሔር አለያም አካባቢ መዳረስ አለበት>> የሚሉ የተለያዩ ቡድኖችን አዋቅረው በየፊናቸው ቅስቀሳ እያደረጉ መሆናቸው ተመልክቷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ-ዓዋዲና ቀኖና ጠብቆ ራሱ ሊያስፈጽመው በሚገባው ታላቅ ሀይማኖታዊ ጉዳይ መንግስት ዛሬም እንዳለፈው ጣልቃ በመግባት ቤተክርስቲያንን በኢህአዴግ ፕሮግራም ለመምራት መሞከሩ ፤በርካታ የእምነቱን ተከታዮች ከወዲሁ እያስቆጣ ይገኛል።
ይህ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና አቋም ፤ በአገር ቤት ያለውንና ስደተኛውን ሲኖዶስ በማስማማት፦ ቤተክርስቲያንን ወደ አንድ ለማምጣት ለረዥም ጊዜ ሲደከምበት የቈየውንና ወደ መፍትሄ ጫፍ እየደረሰ ያለውን የእርቀ-ሰላም ሂደት እንዳያጨናግፈው፤ ከፍ ያለ ስጋት አሳድሯል።
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት፦መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በግልጽ ቢደነገግም ፤የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት 21 ዓመታት በተደጋጋሚ በሀይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ይታያል።
አንጋፋው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፦ <የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት፤ የተፃፈበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አላወጣም>ማለታቸው አይዘነጋም።