ጥቅምት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጲያ የሸሪያ ሕግ እንዲታወጅ የኢትትዮጲያ ሙስሊሞች አለመጠየቃቸውን፤ በኢትዮጲያ ያለው ነባራዊ ሁኔታም ይህንን ጨርሶ እንደማይፈቅድ፤ አንድ የእስልምና ሐይማኖት ምሁር ገለጹ።
በሸሪያ ሕግ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን የሰሩትና የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ኢማም የሆኑት ሼህ ካሊድ መሐመድ ኡመራ ለኢሳት እንደተናገሩት ሸሪያ ሕግ ተግባራዊ የሚሆነው በሙስሊሙ ላይ ብቻ እንደሆነም አመልክተዋል።
እስልምና መቻቻልን እንደሚሰብክ አጥብቀው የተናገሩት ሼህ ካሊድ መሐመድ ኡመር፤ ነብዩ መሐመድ ክርስቲያኖችን በመስጊድ ውስጥ ሃይማኖታቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ ያደረጉበትን ክስተት በአብነት በማውሳት፤ የእስልምና መሰረቱ የሌሎቹንም መብት በማክበር ላይ የተመሰረተ እንደሆንም አብራርተዋል።
ዕምነትን በሃይል መጫን አይቻልም፤ በሃይል ሠውነትን እንጂ ልብን መግዛት አይቻልም ሲሉም አስረድተዋል።
የኢትዮጲያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ፤ ክርስቲያኖችም በአጋርነት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀረቡት ሼህ ካሊድ መሐመድ ኡመር፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በዋልድባ ላይ የሚያነሱትንም ጥያቄ ሙስሊሞች ሊደግፉት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጲያ የጋራ መርከባችን ነች እንዳትሰምጥ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን ሲሉም ጥሪ እቅርበዋል።