ጥቅምት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተለምዶ አሮጌው ቄራ በሚባለው አካባቢ ላለፉት 20 እና 30 አመታት የቀበሌ እና የወረዳ ህጋዊ እውቅና ኖሮአቸው በመጠለያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 51 አባዎራዎች እና እመዎራዎች ባለፈው ቅዳሜ ያለምንም ምትክ ቤታቸውን አፍርሰው የቤት ቁሳቁሳችንን ሁሉ ወረሱብን በማለት በአራዳ ክፍለከተማ አስተዳዳሪ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ፖሊስ ሰልፉን በትኖ ተወካዮቻቸው የአስተዳደሩን ሃላፊዎች እንዲያነጋግሩ አደርጋለሁ በማለት ለማረጋጋት ሞክሯል።
በተቃውሞው ሰልፍ ተማጽኖ ያቀረቡት ወደ 300 የሚጠጉ እጅግ በኑሮ የተጎሳቆሉ እናቶች ፣ አሮጊቶች፣ ሽማግሌዎች እና የትምህርት ቤት ዩኒፎርም የለበሱ እና ዩኒፎርም ያልለበሱ ታዳጊ ተማሪዎች ናቸው ።
አንዳንድ ታዳጊ ልጆች ” ባለፈው ቅዳሜ ዩኒፎርማችንን ቤት ውስጥ አስቀምጠነው ስለነበር ፣ የአራዳ ክፍለ ከተማ አፍራሽ ግብረሀይል ዩኒፎርማችንን ወስዶታል ፣ ዛሬ ወደ ዚህ የመጣነው ያለዩኒፎርም እና ደብተር መማር ስለማንችል ነው” ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።
ለሸራተን ሆቴል ማሰፋፊያ ሲባል በአካባቢው ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አለበቂ ዝግጅት ቀደም ሲል የተነሱ ሲሆን፣ የግል ይዞታ ለነበራቸው ነዋሪዎች ከከተማ ዳር ከገበሬዎች መሬት ተነጥቆ እንደተሰጣቸው ይታወሳል። ይሁን እንጅ ቤታቸውን እንዲሰሩ የተሰጣቸው ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ ቀደም ሲል የነበራቸውን አይነት ቤት ሊያሰራላቸው ባለመቻሉ ችግራቸውን ለመንግስት ባለስልጣናት እና ለመገናኛ ብዙሀን ደጋግመው ቢያሳውቁም መፍትሄ አላገኙም።
በሁለተኛ ደረጃ የገንዘብ አቅም ላላቸው ደግሞ የኮንዶሚኒየም ቤት ቅድመ ክፍያውን እና ወርሀዊ የባንክ እዳውን እየከፈሉ በሞጆ፣ ቃሊቲ ፣ገላን፣ ጎተራ፣ ሀያት፣ ሳሚት እና ሌሎች ቦታዎች እንዲበተኑ ተደርጓል ። አንድ የተቃውሞው ሰልፍ አስተባባሪ ለዘጋቢያችን እንደገለጡት ደግሞ አቅም ለሌላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩ የሆነ የቀበሌ ቤት ሰጥተዋቸዋል። “እኛን” ይላሉ አስተባባሪው ” ዛሬ ነገ ሲሉ ቆይተው ቅዳሜ እለት ምንም ባልተዘጋጀንበት ሁኔታ በአስፈራሽ ግብረ ሀይል በላያችን ላይ ቤታችንን አፍርሰው የቤታችንን ቁሳቁስ ሁሉ ወርሰዋል።”
አስተባባሪው አክለውም ” ዛሬ የምናደርገው ያልተፈቀደ ታቀውሞ ሲሆን ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት የትምህርት ደብተሮቻቸውን፣ መጽሀፎቻቸውን እና እኛም አብስለን የምንበላበትን እቃዎች እንኳን እንዲመለሱልን ለመማጸን ነው “ብለዋል ።
የወረዳው አስተዳዳሪ የተቃውሞ ተማጽኖ የሚያሰሙትን በኑሮ የተጎዱ ዜጎችን ብሶት ካደመጡ በሁዋላ ” እኔ በእኔ አቅም ምን ላደርግላችሁ እችላለሁ ፣ ከቦታው እንድትለቁ ከተጠየቃችሁ ቆይቷል ፣ የበላይ አካላትን አነጋግሩ፣ እኔ መፍትሄ የለኝም” በማለት ወደ ስራቸው ተመልሰዋል።
“መልስ ካልሰጡዋችሁ ምን ልታደርጉ አስባችሁዋል?” በማለት ዘጋቢያችን ላቀረበላቸው ጥያቄ አንድ በእድሜ የገፉ ሰው ሲመልሱ ” እንግዲህ ያው ልጆቻችንን እና በእድሜ የገፉ ወላጆቻችንን ይዘን ጎዳና ላይ እንወጣለን፣ ከቅዳሜ ጀምሮም ተሰባስበን ጎዳና ላይ ነው ያለነው ፣ እንግዲህ ቤተሰብ ተይዞ ጫካ አይገባ ” በማለት መልሰዋል።