አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባፉለት 21 አመታት ከድህነት ወለል በታች የነበረውን ህዝብ ከ38.7 ወደ 29.6 በመቶ መቀነስ ችለናል ሲሉ ተናገሩ

መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመጨረሻም፤ የኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባፉለት 21 አመታት ከድህነት ወለል በታች የነበረውን ህዝብ ከ38.7  ወደ 29.6 በመቶ መቀነስ ችለናል ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዛሬ ለተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክርቤቶች አባላት በጋራ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ መንግስት አመታዊ በጀቱን ለመሸፈንና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም፤ በብድርና በእርዳታ ገንዘብ ሲረዳ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተጻራሪው ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ ወደ 29.6 ከመቶ መቀነስ መቻሉን የተናገሩ ሲሆን፤ በ2012 የተደረገ አለምአቀፍ ጥናት ግን በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ ቁጥር 35 ሚሊዮን ወይም 44 ከመቶው እንደሆነ ያሳያል።

የአለም የገንዘብ ካርታ የተሰኘ ድርጅት ጥናት እንዳመለከተው፤ 12 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በወጉ በልቶ ለማደር በሚቸገርበት ደረጃ ላይ ወይም አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልግበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዛሬ ስራውን በጀመረው ፓርላማ ላይ የተናገሩት ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ለልማትና ለእድገት የሚደረገው ርብርብ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ በዚህ አመት በቀበሌዎችና በወረዳዎች በሚደረገው የማሟያ ምርጫ ለዴሞክራሲ እድገት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

ዛሬ የተከፈተው የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ስነስርአት ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ሌሎች ህጻናት ባቀረቡት የብሄር ብሄረሰቦች መዝሙር ተጠናቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide