መስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ሲፒጄ መግለጫ፤ ጋዜጠኛ ማርቲ የታሠረችው፤ የትናንት አርቡን የሙስሊሞች ተቃውሞ በአንዋር መስጊድ በመገኘት የዘገባ ሽፋን እየሰጠች ባለችበት ጊዜ ነው።
ሰልፈኞቹ፤’በመጪው እሁድ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫን ለማካሄድ መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል’ በማለት ተቃውሟቸውን ለማሰማት የወጡ መሆናቸውን ፤ሲፒጄ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችን በመጥቀስ በመግለጫው ጠቁሟል።
በስፍራው ዘገባዋን እያጠናቀረች የነበረችውጋዜጠኛ ወልፍ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳ የቀረጸቻቸውን ቃለ ምልልሶች እንድትደመስስ መደረጓን የጠቀሰው ሲፒጄ፤ ከዚያም ምንም ክስ ሳይመሰረትባት መለቀቋን አመልክቷል።
ባለፈው ግንቦት ወር የቪኦኤው ፒተር ሀይንላይን የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ እየዘገበ ሳለ እንዲሁ ከአንዋር መስጊድ በፖሊሶች ወደ ማዕከላዊ ተወስዶ ከታሰረ በሁዋላ በማግስቱ መፈታቱ ይታወሳል።
ከዚህም ሌላ በተያዘው ሳምንት የደህንነት ሀይሎች ለቪኦኤ የአማርኛው ክፍል ቃለ-ምልልስ የሰጡ ኢትዮጵያውያንን በማዋከብ ላይ መሆናቸውን፤ ጣቢያውን ዋቢ በማድረግ ሲፒጄ አመልክቷል።
እንዲሁም በተለያዩ ጉዳየች ዙሪያ ከቪኦኤ ጋር የተነጋገሩ ኢትዮጵያውያን እየታሰሩና እየተዋከቡ መሆናቸውን መግለጫው በዝርዝር ያሳያል።
<<የመንግስት አመራር አዲስ የመቻቻል ባህል እንዲያመቻች እና ያለፈውን ጫና የመፍጠር ዘዴ እንዲያቆም እንጠይቃለን>>ብለዋል-የሲፒጄ የምሥራቅ አፍሪቃ አማካሪ ቶም ሩድስ።
ቶም ሩድስ አክለውም፦<<ዜጎች ያለምንም የመታሰር ፍራቻና ጣልቃገብነት ሀሳባቸውን ለጋዜጠኞች የሚገልጹበት፤ጋዜጠኞችም፦ መንግስት የማይወዳቸውን ክስተቶች ጭምር የሚዘግቡበት ድባብ ሊኖር ይገባል>>ብለዋል።
የ ኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተያዘው ዓመት በተደጋጋሚ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ማሰራቸውን የጠቀሰው ሲፒጄ፤ባለፈው ሜይ ጋዜጠኛ ፒተርሀይን ላይን በተመሳሳይ መንገድ መታሰሩን አውስቷል።
በሙስሊም ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሦስት ጋዜጦችም ካለፈው ሜይ ጀምሮ ከህትመት መታገዳቸውን ያወሳው ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ተንከባካቢ ኮሚቴ፤የሙስሊሞች ጉዳይ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው ፤ሙስሊሞች እያሰሙት ስላለው ተቃውሞ በመዘገቡ፤ በአገር ክህደት እና ህዝብን በማነሳሳት ተከሶ በእስር ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ከፍተኛ ኤዲተር የሆነው አከመል ነጋሽና ኮፒ ኤዲተሩ ይስሀቅ እሸቱ ደግሞ መሰወራቸውን ጠቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ስድስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሲፒጄ መግለጫ ያመለክታል።
በሌላ በኩል የአሸባሪነት ክስ ተመስርቶባት በእስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የዓለማቀፍ የሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን የ 2012 ዓመተ ምህረት ልዩ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።
ዓለማቀፉ ፋውንዴሽን በጋዜጠኝነት ሥራቸው ባከናወኑት ተግባራቸውና ሥራቸውን ሢሰሩ የተጋረጡባቸውን ፈተናዎች በጽናት በመቋቋማቸው ባሳዩት ጥንካሬ ከመላው ዓለም ላይ ለሽልማት የመረጣቸውን ሦስት ጋዜጠኞች ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ርዕዮት ዓለሙ ከኢትዮጵያ ፣አስማ አል ጉል-ከጋዛ እና ከድጃ ኢስማኢሎቫ -ከአዘርባጃን የ2012 ዓ.ም የፋውንዴሽኑ ሽልማት አሸናፊዎች ሆነዋል።
የሽልማት ሥነ-ስርዓቱም የፊታችን ኦክቶበር 24 በኒውዮርክ፣ኦክቶበር 29 ደግሞ በሎስ አንጀለስ ይካሄዳል።
ምርጫ 97ትን ተከትሎ ለእስር በተዳረገችበት- የመጀመሪያና ብቸኛ ልጇን የተገላገለችው ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ቀደም ሲል ለዚህ ሽልማት መብቃቷ አይዘነጋም።
እንዲሁም፤በእስር የሚገኘው የሰርካለም ባለቤት እስክንድር ነጋና የ ኢሳቱ ሢሳይ አጌና የ2012 እና የ2011 የፔን የመፃፍና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ፤ የ አውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ደግሞ የሲፒጄ የ 2012 ሽልማቶች አሸናፊዎች መሆናቸው ይታወሳል።
ብዙዎች ፤መንግስት በአገር ክህደት፣ አመጽ በማነሳሳት እና በሽብርተኝነት የሚከሳቸው የ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለእንደዚህ አይነት ታላላቅ ሽልማት መብቃታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ማንነት ለዜጎቹ ብቻ ሳይሆን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ግልጽ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
ሙያዊ የጋዜጠኝነት ተግባሩን በመወጣቱ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተበት የአዲስ ነገሩ ማኔጅንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ በቅርቡ ባስነበበው ጽሁፍ ፦”ሽብርተኛ ያልሆናችሁ እጃችሁን አውጡ!”ማለቱ ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide