በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ተደስታችኋል የተባሉ 6 ኢትዮጵያውያን ታስረው፤ አንዱ የ7 ዓመት እስራት እንደተፈረደበት ታወቀ

መስከረም ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ምንጮቻችን ከሥፍራው እንደገለፁት ከሆነ፣ የአቶ መለስ ሞት ይፋ በተደረገበት ሰሞን፤ በቤታቸው ውስጥ ተሰብስበው የነበሩት ወጣቶች የታሰሩት፤ በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ደስታችሁን ገልጣችኋል፤ ጨፍራቸኋል፤ በሚል ሰበብ እንደሆነ ታውቋል።

የታሰሩት ወጣቶች በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን፣ ከእስረኞቹ ውስጥ አህመድ የተባለው ወጣት፤ የ7 አመት እስራት እንደተፈረደበትና፤ የተቀሩት አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ኢሳት ባለፈው ሣምንት በመተማ በአቶ መለስ ሞት ደስታችሁን ገልፃችኋል የተባሉ 120 ሰዎች መታሰራቸውን መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ በደቡብ ኢትዮጵያም በደቡብ ኦሞ ዞን፤ በአሪ ወረዳ የሚኖሩ 80 አርሶ አደሮች፤ “መለስ ዜናዊ እንኳን ሞተ አናዝንም” ብለዋል ተብለው መታሰራቸውና በወረዳው አቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባቸው መዘገባቸን ይታወሳል።

500 የሲኖ ከባድ መኪናዎች፤ ለቡ በሚገኘውና፤ የወ/ሮ አዜብ መስፍን እንደሆነ በሚነገረው የመስታውት ፋብሪካ መሬት ላይ፤ ለእይታ እንደቀረቡ ከአዲስ አበባ የደረሰን መረጃ አመለከተ።

እነዚህ እያንዳንዳቸው 940 ሺህ ብር የሚያወጡ መኪኖች የተገዙት ለኦሮሚያ ክልል እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ የመኪኖቹ ርክክብ የተፈፀመው ግን በሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካ መሬት ላይ ሳይሆን፤ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ብዙ ድርሻ እንዳላቸው በሚነገረው የመስታውት ፋብሪካ መሬት ላይ እንደሆነ ታውቋል።

አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ከጅቡቲ ወደኢትዮጵያ ዕቃ ለሚያመላልሱ 2000 የጭነት መኪናዎች መግዢያ 5 ቢሊዮን ብር ብድር እንደፈቀዱ ኢትዮጵያን ሪፖርተር እንደዘገበ የሚታወስ ሲሆን፣ እነዚህ 500 ሲኖ ትራኮች በብድር ገንዘብ በግልፅ ጨረታ በሕጋዊ አስመጪና ላኪዎች ይገዙ አይገዙ የሚታወቅ ነገር የለም።

በሌላ ዜና፤ የአዳማ/ናዝሬት ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፤ በአድዋ የሚገኝ ጫማ ፋብሪካን ማሽኖች ገዝቶ፤ ክፍያውን ከፈጸመ ወራት ቢያልፍም፤ በአድዋ የሚገኙት ማሽኖች እስካሁን ወደናዝሬት እንዳልተወሰዱ ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ዘገቡ።

ምንጮቻችን እንደዘገቡት፤ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጆች ማሽኖቹን ለማምጣት በሚል ሰበብ ወደ አድዋ ተጉዘው፤ የአድዋ አካባቢ ሕዝብ ማሽኖቹ አይነቀሉም ብሎ ከለከለን በሚል ሰበብ ባዶ እጃቸውን እንደተመለሱ ታውቋል።

በተጨማሪም የአዳማ ጨርቃጨርቅ አስተዳዳሪዎች ሰራተኛውን ሰብስበው ለጊዜው ጫማዎቹ በአድዋ እየተመረቱ፤ በአዳማ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንደሚሸጡ ለሠራተኞቹ የተናገሩ ሲሆን፤ በግዢው ሁኔታና በፋብሪካ ማሽኖቹ አለመዛወር ጥያቄ የሚያነሱ ሰራተኞች ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው እንደሆነ ታውቋል።

አድማጮቻችን በአዳማ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ስላለው ሙስናና ጭቆና እንዲሁም በጋፋት ኢንጂነሪንግ ስለሚፈፀሙ ተመሳሳይ በደሎች ከኢትዮጵያ ሰፊ መረጃዎች የደረሱን ሲሆን፣ ሙሉ መረጃውን በሚቀጥለው ሣምንት እንደምናቀርብላችሁ እንገልጻለን።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide