መስከረም ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ ዛሬም በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በሚገኙ መስጊዶች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ምርጫው ግን በተያዘለት መርሀ ግብር እሁድ መስከረም 27 ቀን እንደሚቀጥል፤ ባለቤትነቱ የኢህአዴግ የሆነው፤ ፋና ብሮድካስቲንግ፤ በመንግስት የሚደገፈውን የእስልምና ጉዳዮች የፈተዋና የደእዋ ም/ቤት ጠቅሶ ዘገበ።
ከአዲስ አበባ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የተቃውሞ እንቅስቃሴው በአዲስ አበባ በሚገኙ መስጊዶች፤ እንዲሁም በሻሸመኔና ከሚሴ፤ በሀርቡና በሌሎችም ስፍራዎች ቀጥሎ አንደዋለም ምንጮቻችን ነግረውናል።
በተለይም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድን ጨምሮ ብዙዎቹ መስጊዶች ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ መሳሪያ በታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተከበው የዋሉ ሲሆን፤ መሳሪያ በያዙት ፖሊሶች ያለተሸበረው ህዝበ-ሙስሊም ከጠዋቱ 5 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በመስጊዱ ተገኝቶ፤ ተቃውሞውን ቢጫ ካርዶችና ወረቀቶችን በማውለብለብ፤ እንዲሁም ተክቢራ በማድረግ እንዳካሄደ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሕዝብ በተጥለቀለቀው አንዋር መስጊድ የመስኪዱ ኢማም ባደረጉት ንግግር፤ ከስምንት ወር በላይ ሰላም አሳጡን ያላቸው ሰዎች ላይ እርምጃ በመውሰዱ መንግስተን አመስግነው ሲናገሩ፤ ከመስጊድ ውስጥም ውጪም ያለው ህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማት ንግግራቸውን እንዳቋረጣቸው ለማወቅ ተችሏል።
በኢማሙ ንግግር የተከፋው ህዝብ ከወትሮው በተለየ መልኩ፤ ተቃውሞውን ከሰላት በፊት፤ በኢማሙ ንግግር መሀል ጀምሮ፤ ከሰላት በሁዋላም፤ ቀጥሎ እንደዋለ ታውቋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ከመስጊድ ውስጥም ከመስጊድ ውጪም በከፍተኛ ድምጽ ተቃውሞውን አሰምቶና ቢጫ ካርዱን አሳይቶ፤ በመጪው እሁድ የሚደረገው ምርጫና ተመራጮች እነደማይወክሉት ገልጾ፤ ተቃውሞ ከሰዓት በሁዋላ 8 ሰዓት ላይ እንዳበቃ ምንጮቻችን ዘግበዋል።
በዛሬው እለት የነበረውነው ተቃውሞ ሲዘግብ የነበረ የውጭ ጋዜጠኛም እንደታሰረችና የመቅረጫ መሳሪያዎቿ እንደተሰዱባት መረጃ የደረሰን ሲሆን፤ የጋዜጠኛዋን ማንነትና ዜግነት እንደደረስን እናቀርብላችኋለን።
በተያያዘ ዜና ተቃውሞው በሌሎች ከተሞችም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፤ በከሚሴ፤ የመንግስት ባለስልጣናት ህዝቡን በዚህ ሳምንት ሰብስበው ደርግ በተቃዋሚዎች ላይ ቀይ ሽብር እንደፈጸመው፤ እናንተም ከእሁዱ ምርጫ በሁዋላ ትመታላችሁ እንዳሏቸው፤ ከኢትዮጵያ ያነጋገርናቸው ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
ባለቤትነቱ የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት (ኤፈርት) የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ፤ ምርጫው በተያዘለት መርሀግብር መሰረት በመጪው እሁድ በየወረዳና ቀበሌ ጽ/ቤቶች ውስጥ በተቋቋሙ 12 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቀጥል የዘገበ ሲሆን፤ ምርጫውን ህገወጥ ነው ብለው የሚቃወሙት ሙስሊሞች ግን በምርጫው እንደማይሳተፉና፤ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት፤ እንዲሁም ተቃውሟቸውን በተለያየ መልኩ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከሚገኝ ሙስሊም ጋር ያደረግነው ሙሉ ቃለምልልስ በዛሬው የኢሳት ሬድዮ እንድታዳምጡት እንጋብዛለን።