መስከረም ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ እንደገለጠው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተ መንግስቱን ለቀው ባለመውጣታቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ቦሌ ከሚገኘው ቤታቸው ጠዋት እና ማታ ሲገቡና ሲወጡ መንገድ እየተዘጋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እየተፈጠረ ከመሆኑም በላይ ከአሁኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች እያስመረሩ ነው፡፡
በርግጥ ሥራቸውን ጠ/ሚኒስትር ቢሮ እየገቡ በመስራት ላይ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ወ/ሮ አዜብ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ቢገለጽም ጉዳዩን ከነጻ ወገን ለማጣራት ያደረግነውጥረት አልተሳካም፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ቃለመሃላ ከፈጸሙ በኃላ ወዲያውኑ የተወሰዱት ወደ ቤተመንግስት እንደነበር በእርሳቸው የህይወት ታሪክ ላይ የተጻፈው “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ ” የሚለው መጽሀፍ ያመለክታል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን እስካሁን ድረስ ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ቤተመንግስቱ አልገቡም::
በቤተመንግስቱ ቅጥር ግቢ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ባለው ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለመግባት አቶ መለስና ቤተሰባቸው ባይታደሉም ህንጻው እየተጠናቀቀ በመሆኑ አቶ ኃለማርያምና ቤተሰቦቻቸው በቅርቡ ይረከቡታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት ያልተቀበሉት በርካታ የኦህዴድ ከፍተኛ የአመራር አባላት የማእከላዊ ስብሰባቸውን በአዳማ ከተማ እያካሄዱ ነው።
የስብሰባውን ሂደት በተመለከተ መረጃዎች እንደደረሱን እናቀርባለን።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide