የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የፍኖተ ነጻነት እግድ እንዲነሳ በድጋሚ ጠየቁ

መስከረም ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በመንግስት ቀጥተኛ ትእዛዝ የታገደው የፓርቲው ልሳን የሆነው  ፍኖተ ነጻነት እንደገና ስራውን እንዲጀምር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቀዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዋና ጸሀፊው አቶ አስራት ጣሴ፣  የብሄራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ አቶ ትእግስቱ አወሉ፣ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አባል አቶ ስዩም መንገሻ፣ እና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራ ናቸው።

ዶ/ር ነጋሶ ” መንግስት ህገመንግስቱን አያከብርም፣ አንቀጽ 30 ማንኛውም ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ ሊሰበሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግና አቤቱታ ለማቅረብ መብት እንዳለው የሚደነግግ በመሆኑ ዘመቻ ነጻነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያካትታል ብለዋል። የጋዜጣዋን ህትመት ለማስቀጠል እኛ እስከ ፍርድ ቤት እንሄዳለን ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፣ ፍትህን ባያገኙም ሁኔታውን ለታሪክ እና ለትውልድ ለማስቀረት ሲሉ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚሄዱ ገልጠዋል።

ማተሚያ ቤት በማቋቋም ጋዜጣውን ለማተም እቅድ እንዳላቸው የገለጡት ዶ/ር ነጋሶ፣ ይህም ቢሆን ግን መንግስት በፈለገው ጊዜ ሊወርሰው ስለሚችል ዋስትና ሊሆን እንደሚይችልና መፍትሄው የስርአቱን አጠቃላይ ሁኔታ መቀየር መሆኑን ተናግረዋል።

 

በመንግስት የታፈነው ሀሳብን የመግለጽ ሰዋዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ነው ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፣ ከምርጫ 1997 በሁዋላ ጆሞ አካባቢ፣ በሀና ማርያም፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ኮተቤ ለገጣፎ፣ ለገደምቢ ቤቶች እየፈረሱ፣ የማርያም አራስ፣ እመጫቶች፣ ሴቶችና ህጻናት ፣ አሮጊት ሽማግሌዎች፣ ወደ ጎዳና እየተበተኑ ቢሆንም ዛሬ ይህን የሚዘግብ ጋዜጣ አለመኖሩን ዶ/ር ነጋሶ ገልጠዋል።

ዶ/ሩ በማያያዝም ” በጎንደር እስቴ ወረዳ ብዙ ሰዎች መብታቸውን በመጠየቃቸው በግፍ ታስረዋል፣ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ኮከበ ጽበሀ ትምህርት ቤት አምና የመብት ጥያቄ አንስታችሁዋል የተባሉ 8 መምህራን ከስራ ተባረዋል፣ በለገጣፎ የመንግስት እና የመስተዳድሩ ሀላፊዎች መሬት ከነዋሪውና ከገበሬው በገፍ እየነጠቁ ለሀብታሞች በመቸብቸብ የግል ካዝናቸውን እየሞሉ ነው፤ መንግስት ያለ አይመስልም” ብለዋል።

ዋና ጸሀፊው አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው የነጻነትና የመብት ጥያቄ መፍትሄው የማተሚያ ቤት ማቋቋም አይደለም በማለት ከጋዜጠኞች የቀረቡ ጥያቄዎችን የመለሱ ሲሆን፣ መቀጠል ያለበት የመብት ትግል ነው በማለት መፍትሄውን አስቀምጠዋል።

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው ጋዜጣችን ከህትመት የተከለከለችው 20 ሺ ቅጂ ማሳተም ስንጀምር እና ህዝቡ በደንብ ማንበብ ሲጀምር ነው ካሉ በሁዋላ፣ “ለአጭር ጊዜ እቅድ ጋዜጣችን እንዲታተም ማንኛውንም ሰላማዊ ትግል እያደረግን ነው” ሲሉ አክለዋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው የመንግስት አመራር አባላት የአቶ መለስን ራእይ እናስፈጽማለን እያሉ ነው፣  ስሊዚህ ወከባው፣  አፈናው የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ፣ የዲሞክራሲ መጥፋት ፣ የዜጎች ስደት ፣ እስር ፣ ግድያ ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መዳፈን እና ጋዜጠኞችን ማሰደድ ፣ ማሰር ይቀጥላል ማለት ነው” ካሉ በሁዋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት ቢኖሩ የሚያስተካክሉት ጥቂት ነገር እንኳን ዛሬ እድሉ አይገኝም ምክንያቱም እራሳቸውን አልፈዋልና እነዚህ ራእይ አስፈጻሚዎች ይህን ሊያውቁ አይችሉም፣ መለስ ብለው ሊጠይቁዋቸው፣ እንኳን አይችሉም ሞተዋልና፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ እዚህ መጥቶ የሚቀርጸው ለጋዜጠኝነት ዘገባ ሳይሆን ለአቃቢ ህግ ክስ እንዲያበጅ ነው፣ እባካችሁ ኢቲቪዎች ይህን እንኳን ሳታዛቡ ዝግቡ ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለአገዛዙ አይመቹም፣ ባገዛዙ ላይ ከፍተኛ ትችት ያቀርባሉ የተባሉ ጋዜጦች በሰበብ አስባቡ ከገበያ እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide