(Sept 14) በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጪ ግንባር (ኦብነግ) እና በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት መካከል የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የሰላም ድርድር እየተካሄደ በነበረበት ወቅት፤ ባለፈው አርብ 17 ንጹሀን የኦጋዴን ተወላጆች መገደላቸውና 14 ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸው ታወቀ።
አቶ ሀሰን አብዱላሂ፤ በኦብነግ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ሀላፊ፤ ከኢሳት ጋር ባደረጉት አጭር ቃለምልልስ፤ ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠው፤ የአሁኑን ግድያ ለየት የሚያደርገው ግድያው የተፈጸመው የ7 አመት ህጻንን ጨምሮ፤ በመንግስት ቁጥጥር በእስርቤት በሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ላይ ጭምር መሆኑ ነው ብለዋል።
ባለፈው አርብ ጳጉሜን 1 ቀን በዋርዴር ዞን በዴኔት ወረዳ በቆሪሌ ቀበሌ ገ/ማህበር ሜሪጲብሶ በተባለ ቦታ፤ የመንግስት ወታደሮች ህጻናትን ጨምሮ ሴቶችና አዛውንቶችን የኦጋዴን ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ምክንያት ባሰቃቂ መንገድ እንደገዷላቸው ተናግረዋል።
ከተገደሉት ውስጥ 17 ሰዎች ውስጥ፤ በእስርቤት ይገኙ የነበሩ እስረኞች እንዳሉበትም የታወቀ ሲሆን፤ የመንገስት ጦር ህዝቡን በጅምላ ሲቀጣ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ሀሰን፤ በእስር ቤት የነበሩ እስረኞችን አውጥቶ መግደል ግን ከዚህ በፊት ያልተለመደ ነው ብለዋል።
ባንድ በኩል እየተካሄደ በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሀን ህዝብ በጅምላ መገደሉን አጥብቀው የተቃወሙት አቶ ሀሰን አብዱላሂ፤ ድርድር እየተካሄደ ነው ማለት ስምምነት ላይ ተደርሷል ማለት ስላልሆነ፤ የኦብነግ ሰራዊት ከኢህአዴግ ሰራዊት ጋር መፋለሙን ይቀጥላል ብለዋል።
የኢህአዴግ መንግስት የምንታገልለትን ህዝብ መግደሉን ከቀጠለ ግን፤ ድርድሩን መቀጠል አንችልም ሲሉም አስጠንቅቀዋል።