በሙስሊሞች ለተቃውሞ መሰባሰብ ምክንያት ፍርድ ቤት ችሎቱን በተነ

መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሀሙስ መስከረም 3 ቀን 2005 ዓም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ችሎት ከሰአት በሁዋላ በማእከላዊ እስር ቤት የሚገኙትን የኢትዮጵያን ሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙትን የተለያዩ መስኪዶች ኢማሞች እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ላይ ሊሰየም የነበረውን ዝግ ችሎት እጅግ በርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በጊዮርጊስ ዙሪያ በመሰባሰባቸው ህዝባዊ ቁጣ ይፈጥራል በሚል ስጋት ላልተወሰነ ጊዜ አራዘመው።

ከሰአት በሁዋላ ችሎት እንደሚቀርቡ ከጠበቆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው የሰማው ማህበረሰብ ከጥዋት ጀምሮ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ችሎቱ ዙሪያ እና ጊዮርጊስ አካባቢ በማጥለቅለቃቸው ስጋት የገባው የኢህአዴግ መንግስት በርካታ ቁጥር ያላቸውን የፌደራል ፖሊሶች የአደጋ ጊዜ መከላከያቸውንና የመስታውት ጋሻቸውን ይዘው በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አጠገብ በአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ ግቢ ውስጥ በተጠንቀቅ ተዘጋጅተው ታይተዋል።

በፌደራል ፖሊሶች ሽርጉድ የተበሳጩት የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊያሰሙ ሲሉ ፍርድ ቤቱ ችሎቱን ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፋለሁ በማለት ችሎት ለመታዘብ የመጡትን ቤተሰቦች እና ሙስሊሞች ከፍርድ ቤት እና  ከጊዮርጊስ ዙሪያ በትራፊክ  እና በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ከበተኑ በሁዋላ እስረኞቹን በሽፍን መኪና ወደ ማእከላዊ እስር ቤት መልሰዋቸዋል። ፖሊሶቹ የእስረኞችን ቀነ ቀጠሮ ነገ መጥታችሁ ከመረጃ ክፍል መረዳት ትችላላችሁ በማለት ሙስሊሙን በማግባባት በትነዋቸዋል።

ዘጋቢያችን በስፍራው በመንቀሳቀስ እንደዘገበው ሁኔታው ረገብ ካለ በሁዋላ አድማ ለመበተን ዝግጁ ሆነው በእሳት አደጋ መከላከያ ጊቢ ተደብቀው የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች በትላልቅ መኪኖች ተጭነው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

አንድ የፍርድ ቤት ሰራተኛም ለዘጋቢያችን እንደገለጡት ችሎቱን ለማስቻል ዝግጁ የነበሩት ዳኞች ቀነ ቀጠሮውን እንዲያሸጋግሩት የተገደዱት በስልክ ከበላይ አካል ትእዛዝ ከመጣላቸው በሁዋላ ነው።

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በነገው የጁመአ ጸሎት በአቶ መለስ ሞት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ተቃውሞ መልሰው ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተቃውሞ ድምጻችሁን አሰሙ የሚሉ የቅስቀሳ መልእከቶች በኤስ ኤም ኤስ ሲሰራጩ መዋላቸው ታውቋል።

ሙስሊሞች ተቃውሞአቸውን አጠንክረው መቀጠላቸው ለአዲሱ አስተዳዳር ከፍተኛ ራስ ምታት ሊሆንበት እንደሚችል ዘጋቢያችን ትዝብቱን አስፍሯል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide