ከኢህአዴግ መሪዎች የሚጠበቀው፤ ላልተመለሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው ሲሉ አቶ ስዬ አብርሀ ተናገሩ

መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ ስዬ ይህን ያሉት  መድረክ በሲያትል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

<ነፍሱን ይማረውና ከ እንግዲህ አቶ መለስ አርፏል፤አልፏል> ያሉት አቶ ስዬ፤ ከ እንግዲህ የሚቋቋመው መንግስት የ አቶ ሀይለማርያም ወይም ከሌሎቹ የ አንዱ ይሆናል እንጂ የመለስ አይሆንም>ብለዋል።

<ተወደደም ተጠላም የምናውቀው ኢህአዴግ ከ እንግዲህ አይኖርም>ሲሉም አቶ ስዬ አክለዋል።

<የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀያ ዓመታት ያገኘውን ተነፃፃሪ ሰላምና ይብዛም ይነስም በዚህ ወቅት ያፈራቸውን ቁሳዊ እሴቶች ሊያጣ አይፈልግም> ያሉት አቶ ስዬ፤በማያሻማ መልኩ ሁኔታዎች ለሰላማዊ ሽግግር እንዲመቻቹለት ይፈልጋል>ብለዋል።

ኢህአዴግ ለዚህ ሁኔታ ከተለመደው የ እኛ እናውቅልሀለን ፖለቲካ የተለየ መንገድ ማሰብ አለበት ያሉት የመድረክ አመራሩ፤የ ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም እውነታውን በጥሞና መመርመር ይገባቸዋል ብለዋል።

“አለ የሚሉትን የ አቶ መለስን <ሌጋሲ>፤መፈክር እና ፎቶ በማንጠልጠል አለያም ዜማ በማዜም ሊያስጠብቁት አይቻላቸውም”ያሉት አቶ ስዬ፤ሁሉንም  እንዳለ እናስቀጥላለን ብሎ መሞከር ሁሉንም ማጣት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ መክረዋል።

አክለውም፦”ነገሩ የ እልህና የቁጭት ሳይሆን የብልህነትና የ አስተዋይነት ጉዳይ ነው፤ለውጥ መኖሩን መገንዘብ እና ይህን የተገነዘበ ሁሉን የሚያሳትፍ መንገድ መቀየስ አስፈላጊ ነው”ብለዋል።

<አሁን በኢትዮጵያ ብቅ ያለው የለውጥ ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተፈጠረ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን> ያሉት የመድረኩ አመራር፤ለውጡን በዚህ ሁኔታ እንቀበለው ካልን መንገዱ የይቅርታ፣የመመካከር፣የፍቅርና የ አንድነት መንገድ ብቻ ነው>ብለዋል።

በስብሰባው የተገኙት ሌለኛው የመድረክ አመራር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የመድረክን ዓለማና እያከናወናቸው ያላቸውን ተግባራት በስፋት አብራርተዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide