ሀገሪቱን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ ይመሯታል ተባለ

ጳጉሜን ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመስከረም ወር 2005 ዓ.ም የኢህአዴግ ምክር ቤት በአቶ መለስ ዜናዊ ምትክ በሚያካሂደው ምርጫ የሚመረጠው
ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ድርጅቱን ለስድስት ወራት ብቻ በጋራ እንደሚመሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን የግንባሩ
ጽ/ቤት ኃላፊ አስታወቁ፡፡
አቶ ሬድዋን ዛሬ ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ቀጣዩ ጉባዔ
ከሁለት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል በሚለው መሰረት ቀጣዩ ጉባዔ ከስድስት ወራት በኃላ
እንደሚካሄድ ጠቁመው እስከዚያ ከአራቱም አባል ድርጅቶች 45 ሰዎች በድምሩ 180 አባላት የተወከሉበት የግንባሩ
ም/ቤት በተጓደሉት አባላት ምትክ ግንባሩን “በጋራ የሚመሩ” ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ይመርጣል
ብለዋል፡፡
“ከስድስት ወራት በኃላ የግንባሩ ጉባዔ ሲካሄድ ሊቀመንበሩና ምክትል ሊቀመንበሩ ብቻ ሳይሆን የሥራ አስፈጻሚና
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ፡፡ከማንኛውም አባል ጋር ወርዶና የጉባዔው አባል ሆኖ ከተመረጠ
ይመረጣል፡፡እስከዚያው ግን የሊቀመንበርነት ቦታ ተጓድሎአል፡፡ተጓደለውን ቦታ የሚመርጠው ጉባዔው ሳይሆን ምክርቤቱ
በመሆኑ በዚሁ መሰረት በመስከረም ወር ይመርጣል፡፡ቀጣይ ስድስት ወር ሲሞላ አዲሱ ሊቀመንበር ሌላ የጉባዔ አባላት
ይሆኑና እንደገና ምርጫ ተደርጎ የሚመረጡ ከሆነ ይመረጣሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን  የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የሰሞኑ ጉባዔ ስላሳለፈው ውሳኔ ተጠይቀው በሰጡት ምላሸ “…የሁልጊዜም
የድርጅቱ መሰረታዊ እምነት ሕዝቡን ወደተሻለ ደረጃ በመውሰድ ላይ ያነጣጠረ ፣የህዝቡን ሕይወት በመቀየር ላይ
ያነጣጠረ፣የሕዝቡን ሕይወት በመቀየር መሰረታዊ የሆነውን ለውጥ በሃገሪቱ ለማምጣት መሰዋዕትነት መክፈል ላይ
ያተኮረ ነው፡፡በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው በተናጠልና በጋራ በሚሰራው ሥራ ዋንኛው ጉዳይ ሃገር የመለወጡ ሥራ
መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡…..በኃላፊነት መሰላሎች ወደላይ ከፍ የሚል ሰው ይበልጥ ጫና
ያርፍበታል፡፡ይበልጥ እንዲተጋና ይበልጥ መሰዋዕትነት እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡በተለምዶ ከዚህ በፊት ድርጅቱ ይል
እንደነበረው ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፡፡ተመችቶህና ደልቶህ የምትተኛበት አይደለም፡፡..በኢህአዴግ ውስጥ
መበላላት፣መገፋፋት፣መጎሻሸም የሚባል ነገር የለም፡፡ይልቅ አጀንዳው ማን ይበልጥ ያስተባብረናል የሚል ነው”
ብለዋል፡፡
ሕዝቡ የጠ/ሚ መለስና የድርጅታቸውን ዓላማዎች ተገንዝቦ በቁጭት ትግላቸውን ለማሳካት ዝግጁነቱን ሲያረጋግጥ ምንም
ጉድለት የለባችሁም ከሚል ስሜት ጸድቶ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ሬድዋን ግንባሩ ችግሮቹን ከተጀመረው ፍጥነት
በላይ በመጓዝ ይፈታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide