ሐምሌ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ደጀ-ሰላም እንደዘገበው፤የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና ራእይ ለትውልድ ፤ በእንግሊዝኛው አጠራር ፦/Vision for Generation/ የተባለው አካል የጥቅም ትስስር የፈጠሩበት የሼራተኑ በዓለ ሢመት ዝግጅት የተከናወነው፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ይኹን አለያም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት፤ እስካሁን አልታወቀም።
በዚሁ የአቡነ ጳውሎስ 20ኛ ዓመት በዓለ-ሢመት ላይ፤ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአብያተ እምነት መሪዎችን፣ አምባሳደሮችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ እንግዶች መታደማቸው ታውቋል።
ይህ ደማቅ ዝግጅት ከጥቅም ትስስር ባሻገር÷ በግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እና ውሳኔዎች ክፉኛ የተጋለጠውን የአባ ጳውሎስን ማንነት ለማደስ የታሰበበት ‹የሕዝብ ግንኙነት› ሥራ ነውም ተብሏል።
“በበዓለ ሢመቱ አከባበር የቀደሙት ፓትርያርኮች መልካም ስምና ዝና በተለያዩ ስልቶች እየተንኳሰሰ ፤በምትኩ በሙስና፣ በኑፋቄ እና በዐምባገነናዊ አሠራር የተበሳበሰው የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የሥራ ክንውን ብቻ “በወደር የለሽነት መሞገሱ ብዙዎችን አሳዝኗል”ብሏል ደጀ-ሰላም።
ድረ-ገጹ እንዳለው፤በበዓለ ሢመቱ ቀን “አንተ የተወገዝኽ ፓትርያርክ ነኽ፤ ሃይማኖት የለኽም!!” ሲሉ አባ ጳውሎስን በመናፍቅነት ያወገዙ ባሕታዊ÷ “ማን ነው የላከኽ?” በሚል፤ ለሳምንት ታስረው ሲደበደቡ ከሰነበቱ በኋላ ተፈተዋል።በዓለ ሢመቱን በማክበር ሰበብ፤ በሚልዮን የሚቆጠር የአብያተ ክርስቲያን ገንዘብ- ወደ ግለሰቦች ኪስ ገብቷል። ከመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም ብቻ ፤ግማሽ ሚልዮን ብር ተወስዷል።በዚህም ሳቢያ ምእመናኑና የገዳሙ አስተዳዳሪ ከመጪው የሐምሌ 19 ክብረ በዓል ገቢ ጋራ በተያያዘ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።
በተያያዘ ዜና በሐምሌው ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አባ ጳውሎስ ማደርያቸውን ቆልፈው “አልሰበስብም” በማለት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥሪ የእምቢታ መልስ በመስጠታቸው ስብሰባው ሳይካሄድ መቅረቱን የጠቆመው ደጀ-ሰላም፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም፦ “የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፍረድ!!” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸው ወደ የሀ/ስብከታቸው መመለሳቸውን አስነብቧል።
ከዚህም በላይ፤ የግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፤ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋራ ስለሚደረገው የዕርቀ ሰላም ንግግር ውሳኔ ያሳለፈበት ቃለ ጉባኤ መጥፋቱም ፤ተገልጿል።
“ በበዓለ ሢመታቸው ቀን “የምንተጋገዝ፣ የምንተማመን፣ ይቅር የምንባባል እንኹን” በማለት የተናገሩት አባ ጳውሎስ÷ ቃለ ጉባኤውን ኾነ ብለው በመሰወር እና ለዕርቀ ሰላም ንግግሩ መቀጠል ጽኑ አቋም የያዙትን አባቶች በመገዳደር ግብዝነታቸውን አሳይተዋል”ያለው ድረ-ገጹ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ የሀገረ-ስብከታቸው ከመመለሳቸው በፊት ቋሚ ሲኖዶሱ፤ ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተለው አደራ ሰጥተዋል”ብሏል።
በኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ታሪክ በየ ዓመቱ ሐምሌ 5 ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ በዓል የሚከበርበት ዕለት ሲሆን፤ አቡነ ጳውሎስ ከተሾሙ ወዲህ ከዚህ ቀን ጋር በማያያዝ በዓለ-ሲመታቸውን ማክበር በመጀመራቸው፤ አሁን አሁን ዕለቱ – በቅዱስ ሲኖዶስ ቀን ሳይሆን “ በፓትርያርኩ በዓለ-ሲመት” ቀን ሲጠራ መስማት የተለመደ ሆኗል።
አቡነ ጳውሎስ ከአወዛጋቢው ሹመታቸው ጀምሮ ምድራዊ ክብርን በመውደድ እና በመሽቆጥቆጥ ከፍተኛ ወቀሳ የሚሰነዘርባቸው ሲሆን፤ ይህም ባህርያቸው መጠኑ እጅግ ከፍ ላለ የቤተክርስቲያን ገንዘብ መውደም ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ከቤተክርስቲያን አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፓትርያርኩ ከዓመት በፊት ፤በርካታ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በእህል ውሀ፣ በሻማ፣ በጧፍና በሌሎች ጥቃቅን መባዎች እጥረት ሳቢያ የቅዳሴ አገልግሎት እስከማስተጓጎል በተገደዱበት ወቅት፤ በመቶ ሺህ ብሮች ወጪ የራሳቸውን ሐውልት በቅፅረ-ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማቆማቸው ፤ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶባቸው መቆየቱ አይዘነጋም።
አቡነ ጳውሎስ ሐውልት ያቆሙት፤ ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ዳግም በመታሰሯ ምክንያት በአገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት በተፈጠረበትና ሌሎች ወገኖች ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ በሚል ላይ ታች በሚሉበት ወቅት ነበር።
ዛሬ 20ኛ ዓመታቸውን በደመቀ-ሁኔታ በሸራተን አዲስ ያከበሩት ደግሞ፤በዋልድባ ገዳም ላይ ፈታኝ ችግር በተጋረጠበት እና አቶ መለስ ዜናዊ በጠና በታመሙበት ጊዜ ነው።
የቤተ-ክርስቲያኗ ምዕመናን ፡_“በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አቡነ ጳውሎስ ምድራዊ ክብርን የሚወድ ፓትርያርክ አልታየም፤ወደፊትም ይነሳል ተብሎ አይታሰብም”ሲሉ ይደመጣሉ።
ትናንት በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ለተከናወነው 20ኛ ሲመተ በዓላቸው በተበተነው የጥሪ ወረቀት ላይ የተቀመጠው የፓትርያርኩ ማዕረግ፦”ብፅዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ፣ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ፣ሊቀ-ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት፣የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣የ ዓለም ሀይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት” የሚል ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide