ሐምሌ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀጣይ አምስት አመታት የስልጣን ድልድል ቅድመ አቋም ግምገማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውይይት በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ 80 በመቶ የኢህአዴግ ሚኒስትሮች ችግር የምፍታት አቅም የላቸውም። ለግምገማ በቀረቡት የተለያዩ መስፈርቶች ብቃት አላቸው የተባሉት አቶ በረከት ስምኦን ሲሆኑ፣ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ አብዛኞቹ ሚኒስትሮች ችግር ፈችዎች አይደሉም ተብለዋል።
ቅድመ አቋም ግምገማውን ያካሂዱት ከአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ ነባር ታጋዮች ናቸው።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሁሉም የስራ ሰአት ማለትም ጧትና ማታ የመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑ፣ ጫናዎችን ተቋቁሞ የመስራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ መሆኑ፣ ለጊዜ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡ መሆናቸው እንዲሁም በሁሉም አካባቢዎች የሚመጡ ሪፖርቶችን አንብቦ በመቀበል ረገድ የተሻሉ መሆናቸው በጥንካሬ ጎን ተይዞላቸዋል።
ይሁን እንጅ ችግሮችን ተቀብሎ መልስ የመስጠት፣ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የሚያስችል አቅም የላቸውም ተብለዋል። እንዲሁም በንባብ ለህዝቡ መረጃ መስጠት፣ ህዝብን በመድረክ ላይ በማነጋገር፣ የብሄር እንድምታዎችን እና የስልጣን
ክፍፍሎችን አይነቶችን የማወቅ እና መረዳት አቅም ውስንነት፣ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታዎች ትኩረት ሰጥቶ በመስራት፣ በጥናት ተመስርቶ አፍሪካን የመምራት ቦታውን በአቅም የመምራት ብቃት ፣ በአገሪቱ እና በአለም ወቅታዊ ጉዳይ የበለጸገ መረጃ
መያዝ እንዲሁም የውሳኔ ሰጪነት ችግር እንደሚታይባቸው ለውይይት በቀረበው የሚኒስትሮች ምደባ ዝርዝር የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ተመልክቷል።
ምክትል ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ደግሞ ችግሮችን ለይቶ ችግር መፍታት ላይ ችግር ያለበት መሆኑ፣ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ትንተናዎችን የመስጠት አቅም የሌለው መሆኑ፣ በሁሉም አካባቢዎች መረጃ ተቀብሎ የመያዝ አቅሙ አነስተኛ መሆኑና በትግራይ ታጥሮ መያዙ፣ በሚመራው ክላስተር ተቋም በቂ እውቀት የሌለው መሆኑ፣ የኢንፎርሜሽን እና መረጃ ደህንነት መገምገም እና አውቆ መምራት ላይ ውስንነት ያለበት መሆኑ፣ ለሃገሪቱ ገጽታ ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ የማይሰራ መሆኑ፣ አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባ መሆኑ፣ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለመስራት ከበቂ በላይ ጊዜ የሚፍልግ መሆኑ፣ መድረክ የመምራት ችግር፣ እንዲሁም ለጊዜ የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ መሆን በድክምትነት የተመዘገበባቸው ሲሆን፣ ለትግል ያላቸው ጽናትና የብሄር ውክልና ያላቸው መሆኑ በጥንካሬ ተይዞላቸዋል።
ም/ል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ የድርጅት ውክልናው ጠንካራ ቢሆንም፣ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ትንታኔዎችን የመስጠት አቅሙ አነስተኛ ነው ተብሎአል። በሁሉም አካባቢዎች የሚሰጡ የስምሪት ስራዎችን የመስራት
ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን በአወንታዊነት ተጠቅሷል። ህዝባዊ ተቀባይነቱ አነስተኛ መሆኑ፣ በጥናት ተመስርቶ ውጤት የማምጣት ብቃቱ አነስተና መሆን፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የበለጸገ መረጃ አለመያዝ፣ ጨናዎችን ተቋቁሞ ለመስራት ፍላጎት አለማሳየት፣ለአንዳንድ ውሳኔዎች ባዳ መሆን የሚሉት በድክመት ተዘርዝረዋል።
ወ/ሮ አስቴር ማሞ የፖለቲካዊ አቅም ውስንነት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት በማሳየት ፣ ኦህዴድን በመቆጣጠር ኦነግን ለመነጠል ያላት ብቃት ውስን መሆን፣ በሁሉም አካባቢዎች አማክላ የተሰጣትን ዘርፍ በመምራት ረገድ አነስተኛ አቅም ያላት መሆን፣
ሲቨል ሰርቪሱን በብቃት ለመምራት አለመቻሉዋ ፣ ለጊዜ የምትሰጠው ዋጋ አነስተኛ መሆን የሚሉት በድክመትነት ከተጠቀሱባት ነጥቦች መካካል ይገኛሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ችግሮችን አጥንቶ ችግር ፊች ስራዎችን በመጠኑ የሚሰራ መሆኑ፣ በማንበብ ለህዝብ መረጃ የመስጠት አቅም ያለው መሆኑ፣ በሁሉም አካባቢዎች የመስራት አቅምና ፍላጎት ያለው መሆኑ፣ በቀጥታ
ህዝቡ ላይ የመድረስ አቅም ያለው፣ በወቅታዊ ጉዳይ የበለጸገ መረጃ ያለው መሆኑን ለአገሪቱ የገጽታ ግንባታ የሚሰራ መሆኑ በጥሩ ጎን ሲጠቀሱለት፣ በጥናት ተመስርቶ ዲፕሎማቶችን የማሰማራት አቅም የሌለው መሆኑ፣ የዲፕሎማሲ ተደራሽነቱ
እሴት በማይጨምሩ በአፍሪካ ሀገሮች የታጠረ መሆኑ፣ ዲፕሎማቶችን ገምግሞ በመምራት ፣ የተጠናከረ ፋይላቸውን በማሳወቅ ፣ ዲፕሎማቶችን ተከታትሎ አስተያየት በመስጠት በኩል ድክመቶች እንዳሉበት ተጠቅሷል። እንዲሁም ጫናዎችን
ተቋቁሙ ለመስራት አቅም የሚያንሰው ፣ በራሱ የማይተማመን እና ሀገራዊ መድረክ የመምራት ችሎታ የሌለው መሆኑ በድክመትነት ተዘርዝሮ ቀርቧል።
ዶ/ር አርከበ እቁባይ ደግሞ ችግር ፈችና ውሳኔ ሰጪነት ላይ፣ በጥናት ተመስርቶ ስራዎችን በመስራት፣ ለሃገሪቱ የገጽታ ግንባታዎች ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ፣ በውቃቲ ጉዳዮች ላይ የበለጸገ መረጃ መያዝ እንዲሁም የፖለቲካ እግሮችን በማወቅና በመረዳት በኩል መልካም ነው ተብሎአል። በድክመትነት ከተዘረዘሩት ውስጥ ሁሉም ክልሎችን እና አካባቢዎችን የተመለከተ እውቀት ማጣት፣ ማን አለብኝነት፣ ከሌሎች ብሄር ድርጅቶች ጋር የመስራት ፍላጎት አለመኖር፣ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን
ለመቅረፍ የሚያስችሉ መድረኮችን አለመምራት፣ አለማዘጋጀት፣ በተሾመበት ቦታ ተከታትሎ ለጠ/ሚኒስትሩ አስተያየት አለመስጠት ፣ ለጊዜ የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ መሆን በድክምትነት ቀርበውበታል።
አቶ በረከት ስምኦን የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መድረኮችን በማዘጋጀትና በመምራት፣ ለህዝቡ መረጃ የመስጠት አቅም፣ በሁሉም አካባቢዎች ሀገራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተሰጠውን ስራ የመስራት ፍላጎት ያለው መሆን፣ ለጠ/ሚኒስትሩ ተከታትሎ አስተያየት የሚሰጥ መሆኑ፣ አገራዊ አቅጣጫዎችን የሚያውቅ የሚረዳና የሚያመላክት፣ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያለው ፣ በጥናት ተመስርቶ አቅጣጫዎችን የመስጠት ብቃት ያለው መሆን፣ በወቅታዊ ጉዳይ በለጸገ መረጃ ያለው መሆን፣ ጫናዎችን ተቋቁሞ የመስራት ብቃት ያለው መሆን፣ ለጊዜ ዋጋ የሚሰጥ፣ ቀጠሮ የሚያከብር፣ በሁሉም የስራ ሰአት የመስራት ፍላጎት ያለው የሚሉት በጥሩ ጎኑ ተጠቅሰውለታል። በድክመት የተቀመጡት ከግለሰብ ባህሪ በተለይም ከመጠጥና ከገንዘብ ብክንነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ከሁሉም ሚኒስትሮች ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ያስወጡት አቶ በረከት መሆናቸው ተመልክቷል።
አቶ አባይ ጸየሃ ለጊዜ ዋጋ የሚሰጡ እና ቀጠሮም አክባሪ መሆናቸው በአወንታዊነት የተያዘላቸው ሲሆኑ፣ ችግሮችን አጥንቶ ችግር ፈች ስራዎችን በመስራት፣ በንባብ ላይ የተመሰረተ ለህብረተሰቡ መረጃዎችን በመስጠት፣ በሁሉም አካባቢዎች
ክንዋኔዎችን የመምራት አቅምና ፍላጎት በማሳየት፣ በጥናት ተመስርቶ ፖለሲዎችን በመተንተን፣ ውሳኔ ጽፎ በማቅረብ፣ ለአሀገሪቱ ገጽታ ግንባታዎች ትኩረት ሰጥቶ በመስራት፣ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለመስራት ያለው ፍለጎት በድክመት ተቀምጠዋል። የአማካሪነት
ውክልናው ዝቅተኛ መሆን፣ ድርጅታዊ ውክልናና ተቀባይነት የሌለው መሆኑ፣ የብሄር አንድነቶችን በመረዳት ፣ እንዲሁም ከባለሃብቶች ጋር ያለው ተለጣፊነት በድክመት ቀርበዋል።
አቶ ሬድዋን ሁሴን ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲዎችን የመምራት አቅም እንዳለውና አንደበተ ርትዑ መሆኑ በመልካም ጎን ቢጠቀስለትም፣ ኮሚኒኬሽን መስሪያቤትን አማክሎ በመስራት የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመቅረፍ መድረክ በማዘጋጀት፣ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳውን በመምራት፣ የፕሮፓጋንዳ ይዘቶችንና አይነቶችን ለይቶ በማወቅና በመረዳት፣ ለአገሪቱ ገጽታ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት፣ በወቅታዊ ጉዳዮች መረጃዎችን በፍጥነት ተቀብሎ በማስተላለፍ በኩል ችግር እንዳለበት ተቀምጧል። የሚሰጠው
ፖለቲካዊ ውሳኔም ብስለት የተሞላበት አለመሆንና ውሳኔ ሰጪነቱ የዘገየ መሆኑ በግምገማው ተጠቅሷል።
ከሁሉም ሚኒስትሮች ጊዜያዊ የግምገማ ሪፖርት በመነሳት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ሃላፊው አቶ አህመድ አብተው፣ የትምህርት ሚኒሰትሩ ሽፈራው ሽጉጤ በሃላፊነታቸው ላይቆዩ ይችላሉ።