ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል በአለፋ ጣቁሳ ወረዳ በማዳበሪያ እዳ የተያዙ ከ200 በላይ አርሶአደሮች መታሰራቸውን ዘጋቢያችን ገልጧል። ገዢው ፓርቲ ለገቢ ማሰባሰቢያ በሚል በግዴታና በውዴታ ማዳበሪያ በእዳ ሲያከፋፍል ከቆየ በሁዋላ ካለፉት 2 ወራት ጀምሮ አርሶአደሮቹ በአስቸኳይ እንዲከፍሉ ትእዛዝ ወርዶባቸዋል። እዳቸውን ለመክፈል አቅሙ ያጠራቸው አርሶአደሮች በገፍ እየተያዙ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።
አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የጠየቀ ሰው ለኢሳት እንደገለጠው በእስር ላይ ከሚገኙት አርሶአደሮች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፣ አሮጊቶች እና ሽማግሌዎች ናቸው። ጎልማሳ ወንዶችና አዋቂዎች ብዙውን ጊዜ የማዳበሪያ እዳ ወይም ግብር መክፈል ሲቸገሩ ከአካባቢው እንደሚሸሹና በእነሱም ምትክ ሚስቶቻቸው ወይም ወላጆቻቸው ተይዘው እንደሚታሰሩ ይታወቃል።
በሌላ ዜና ደግሞ ከመሬት ጋር በተያያዘ ተቃውሞ አሰሙ አርሶአደሮች 6 አመት እስር ተፈርዶባቸዋል።
በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ከወራት በፊት የግጦሽ መሬታችንን ለኢንቨስተር አንሰጥም በማለት የጎቶ መንደሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ አንድ ፖሊስ መገደሉን እና ሌሎች የወረዳው ባለስልጣናት ቆስለው ማምለጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አርሶ አደሮቹ ለከብቶቻቸው ግጦሽ መሬት ብለው የከለሉትን ቦታ የወረዳው ባለስልጣናት የፈረጃት ጉቶበር ግብርና ልማት የተወሰነ የግል ማህበር ለተባለ አዲስ ማህበር ለመስጠት መወሰናቸው ግጭቱን መቀስቀሱን መዘገባችንን ተከትሎ፣ ግጭቱን አነሳስተዋል የተባሉ 12 ሰዎች ማደኛ ወጥቶባቸው ሲፈለጉ ቆይቷል።
ከእነዚህ አርሶአደሮች መካከል 8ቱ አካባቢውን ለቀው በመጥፋት ከእስራት ያመለጡ ሲሆን አራቱ ግን በቁጥጥር ስር ውለዋል። የዞኑ ፍርድ ቤት ግለሰቦችን ጸረ ልማት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት እና ሽብር ለመፍጠር የተነሳሱ ናቸው በማለት ውሳኔ አስተላልፎአል።
በልማት አደናቃፊነት የተፈረጁት አቶ ውሎቶ ቱላ፣ ወ/ሮ አዶሬ ኬሎም፣ አቶ ሙስጤ ሙጣንስ እና አቶ ዘኒ አባስ ናቸው። ግለሰቦቹ አመጹን ለማስነሳታቸው በቂ ማስረጃ ሳይቀርብባቸው በስድስት አመት እስራት እንዲቀጡ መደረጉን የገለጠው ዘጋቢያችንን፣ ውሳኔው የአካባቢው ነዋሪ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንዳያነሳ እንደመቀጣጫ ተደርጎ የተወሰደ ነው ሲል አክሎአል።
ፍርድ ቤቱ በግለሰቦቹ ላይ የሰጠው ውሳኔ የአካባቢውን ነዋሪዎች አለማስደንገጡን የገለጠው ዘጋቢያችን ህዝቡ በአንድነት በመሆን መሬቱን እየተቆጣጠረ መገኘቱ ማህበሩ ስራውን እንዲያቋርጥ የአካባቢው ሹማምንትም ወደ አካባቢው ለመሄድ እና መሬቱን ለመስጠት እንደፈሩ ዘጋቢአችን አክሎ ገልጧል።