ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2008)
ከሁለት ቀን በፊት ከ30 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ያዋለው የማላዊ መንግስት ተጨማሪ 76 ኢትዮጵያውያንን ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገለጠ።
ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል 33ቱ በእቃ መጫኛ (ኮንቴይነር) ተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቀው ከማላዊ ለመውጣት በጉዞ ላይ ኣያሉ ሊያዙ መቻላቸውን የማላዊ ፖሊስ አስታውቋል።
በስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መበራከት ስታጋቸውን በመግለጽ ላይ ያሉት የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በዕቃ መጫኛ ተሽከርካሪው ውስጥ ከተገኙት በተጨማሪ 43 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በእግር በመጓዝ ላይ እንዳሉ በጸጥታ ሃይሎች ለእስር መዳረጋቸውንም ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በተሽከርካሪ ሲያጓጉዝ የነበረ አንድ የማላዊ ዜጋ ከጸጥታ ሃይሎች በማምለጡ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፍለጋ ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑም ታውቋል።
ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል አንድ ኤርትራዊ መኖሩን የተናገሩት የማላዊ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ስደተኞቹ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ክስ እንደሚመሰረትባቸውም ዛምቢያ ዴይሊ የተሰኘ ሃሙስ ዘግቧል።
ከሁለት ቀን በፊት ወደ ዛምቢያ በተመሳሳይ መንገድ ገብታችኋል ተብለው 34 ኢትዮጵያውያን ተይዘው የነበረ ሲሆን፣ ከስደተኞቹ መካከል አንደኛው በነዋሪዎች ድብደባ ተፈጽሞበት በህክምና ላይ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት የስደገተኞች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ በመሰደድ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል።
በዛምቢያ በተደጋጋሚ ለእስር ከተዳረጉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞች በማላዊ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌና ሌሎች ሃገራትም በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ሰዎችን ለመግታት በድንበር ዙሪያ ቁጥጥርን ቢያደርግም ስደቱ ሊቀንስ አለመቻሉንም የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
በየዕለቱ በዛምቢያ ለእስር በመዳረግ ላይ ስላሉ ኢትዮጵያውያን በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል እስከ አሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።