ሚያዝያ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ይዘው ለመግዛት ባህር አቋርጠው የመጡትን የፋሽሽት ጣሊያን ወታደሮች፣ በአምስት አመት የአርበኝነት ተጋድሎ በማንበርከክ የኢትዮጵያን ነጻነት መልሰው እጃቸው ውስጥ ያስገቡበት፣ 76ኛው የድል በዓል በመላው ኢትዮጵያ ተከብሯል።
አትዮጵያውያን አርበኞች በጎብዝ አለቆች እንዲሁም በጊዜው በነበሩ መሳፍንት እየተመሩ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተደራጅቶ የመጣውንና መላ ኢትዮጵያን ወሮ ለመያዝ አልሞ የመጣውን የፋሽስቱ ቢኒቶ ሙሶሎኒን ጦር በዱር በገደሉ ተፋልመዋል። በአሮጌ ጠመንጃ ዘመናዊ መትረጊሶችንና ታንኮችን ሳይቀር ማርከው የጣሊያንን ጦር መግቢያ መውጫ አሳጥተዋል። ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃች በላይ ዘለቀ፣ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ እና ሌሎችም እውቅ አርበኞች ህዝባቸውን በመምራት ከጣሊያን ወራሪ ሃይል፣ ጣሊያንን በማገዝ በአገር ላይ ክህደት ከፈጸሙት ባንዶች እንዲሁም ከኤርትራ፣ ሊቢያና ሶማሊያ በጣሊያን ተመልምለው ከመጡ ታዛዦች ጋር ተፋልመው የኢትዮጵያን ነጻነት በማስመለስ በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ብቸኛ አገር የሚያደርግ ታሪክ ጽፈው አልፈዋል።
በዚህ የ5 አመታት ጦርነት፣ ጣሊያንን በመክዳት ለኢትዮጵያ ደማቸውን ያፈሰሱ በርካታ የኤርትራ ተወላጆች መኖራቸውን ድርሳናት ያሳያሉ። ለኢትዮጵያ ነጻነት ድጋፋቸውን ያሳዩ አፍሪካውያንና ስማቸው ዘወትር የሚነሳው ሲቪላ ፓንክረስትና አንዳንድ የምእራብ አገራት የነጻነት ፋኖዎችም ተሳትፈዋል።
የጣሊያን ወራሪ ሃይል በአዲስ አበባ የካቲት 12 ፣ በደብረሊባኖስ ገደም እና በበርካታ የአገሪቱ ክፍል እጅግ ዘግናኝ የሚባል ጭፍጨፋ ፈጽሟል። በአየር ላይ የተከለከለ መርዝ በመርጨትም የርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ቀጥፏል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ያልተበገሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ፣ በመጨረሻም የአለም ፖለቲካ መለወጡን ተከትሎ ከስደት የተመለሱት አጼ ሃይለስላሴ ከእንግሊዝ ባገኙት ድጋፍ በመታገዝ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓም አዲስ አበባ ገብተው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራውን በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ አውለብልበዋል።
እነዚህ ጀግኖች አርበኞች የፈጸሙት ወደር የለሽ ጀግንነት የሚታሰብበት አመታዊ በአል፣ በእያመቱ እየተቀዛቀዘ ትውልዱም ስለአባቶቹ ታሪክ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖረው መደረጉ ብዙዎችን ሲያበሳጭ ቆይቷል። በዚህ አመት በአሉ በተሻለ ሁኔታ መከበሩን የሚገልጹት ታዛቢዎች፣ በአሉ በመጪዎቹ አመታት ከዚህ በበለጠ እንዲከበር ትውልዱን ማስተማር እንደሚገባም መክረዋል።