ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በአውሮፓ ፓርላማ ፊት ለፊት ተደረገ

ግንቦት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ግንቦት8፣ 2004 ዓም በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ፊት ለፊት በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተውጣጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል። የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት፣ የሉቅማን የኢትዮጵያውያንና ቤልጂየማውያን ሙስሊሞች ማህበር እንዲሁም በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በጋራ ባዘጋጁት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከጀርመን፣ ስዊድን፣ ሆላንድ፣ ሉክዘምበርግ፣ እንግሊዝና ከሌሎችም አገሮች የመጡ ሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በብዛት ተገኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፈላጭ ቆራጭ እና ዘረኛ አገዛዝ እንደሚያወግዙ ገልጠዋል። በተቃውሞው ሰልፍ ላይ ሲስተጋቡ ከነበሩት መፈክሮች መካከል ” መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው፣ መለስ ዜናዊ አሸባሪ ነው፣ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ የመሬት መቀራመት ይቁም፣ የአውሮፓ ህበረት አምባገነኖችን መርዳት ያቁም፣ በአፋር ክልል የሚታየውን የህዝብ መፈናቀል እንዲሁም በደቡብ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል እናወግዛለን” የሚሉት ይገኙበታል።

በተቃውሞው ላይ ለመገኘት ከመጡት መካከል ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ አንዱ ናቸው። በተቃውሞው ለመሳተፍ የተነሳሱበትን ምክንያት ሲገልጡ እንዲህ ይላሉ።

በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ያሬድ ሀይለማርያም ተቃውሞውን ለማድረግ ያስፈለገው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ነው ይላሉ። አቶ ያሬድ ጥያቄያቸውን ለአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ማቅረባቸውንም ገልጠዋል።

በሌላ በኩል ባሳለፍነው ቅዳሜ በሆላንድ  በአምስተርዳም ከተማ መንግስት ጥቂት ደጋፊዎቹን በድብቅ  ሰብሰቦ ለአባይ ግድብ ድጋፍ እንዲያዋጡ ጠይቋል። ከተለያዩ የሆላንድ ከተሞች ብዙ ሰዎች ይመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከአስራ አንድ ያልበለጡ ቀንደኛ ደጋፊዎች ብቻ መገኘታቸውታውቆአል። የስበሰባው አዘጋጆች ለአባይ ቦንድ ግዢ ህብረተሰቡን የሚያስተባብሩ ሁለት ሁለት ተወካዮች በየከተማው ህዋስ በመጣል ቀጣይነትያለው ስራ ለመስራት በመስማማት፣ የቅስቀሳ ሲዲዎችን በማደል ስበሰባው ተጠናቋል። መንግስት ከመንግስትነት ደረጃ ወርዶ ስብሰባዎችን በድብቅ እና ተቃዋሚዎች እንዳይሰሙት በማድረግ ማካሄድ መጀመሩ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል።

በተመሳሳይ መንገድም በሉክሰምበርግ ባለፈው ሚያዚያ ወር ሊካሄድ የነበረው ስበሰባ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ በማሰማታቸው መሰረዙ ታውቋል። በሉክዘምበርግ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት እንደገለጡት ኤፕሪል 29 ቀን በአባይ ግድብ ዙሪያ ሊካሄድ የነበረው ስብሰባ ኢትዮጵያውያን በመቃወማቸው ለሜይ 29 በድብቅ እንዲተላለፍ ተደርጓል። በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኞች ስብሰባውን የሚቃወሙትን ኢትዮጵያውያንን ስልክ በመደወል ለማግባባት እና ለማስፈራራት ሙከራ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ኢትዮጵያውያኑ እንዳሉት ሜይ 29 ቀን በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያንን ፎቶ ግራፍ በማንሳት ለአገሪቱ የኢምግሬሽን ቢሮ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።

በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አቶ መለስን ለመቃወም ዝግጅት እያደረጉ ነው

አስተባባሪዎች ለኢሳት በላኩት መረጃ ከሁለት ቀናት በሁዋላ  በአሜሪካ  ዋሽንግተን ዲሲ በሮናልድ ሬገን ህንጻ እና በአለም ንግድ ማእከል በሚደረገው አለማቀፍ ግብርና እና የምግብ ዋስትና ላይ ለመካፈል የሚመጡትን አቶ መለስ ዜናዊን ለመቃወም ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

አዘጋጆቹ የባራክ ኦባማ አስተዳደር አቶ መለስን በጉባኤው ላይ እንዲገኙ መጋበዙን ነቅፈዋል። መለስ”  በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ህዝቡን እርስ በርስ በማጫረስ ላይ መሆኑ፣  በብዙ ሺ የሚቆጠሩ እህቶቻችንን ለአረብ አገራት በባርነት እየሸጠ መሆኑ፣ ንጹሀን ዜጎችን በመግደሉ፣ የአገሪቱን ለም መሬት ለውጭ ባለሀብቶች በመቸብቸብ ላይ መሆኑ፣ ነጻ አሳቢ ዜጎችን በማሰር የሚታወቅ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት በመሸጥ የማፍያ ድርጅቶች መሪ በመሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ውድመት ዋናው መሀንዲስ በመሆኑ” በጉባኤው ላይ ለመገኘት የሞራል ብቃቱ የለውም ይላሉ አዘጋጆች።

አዘጋጆቹ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አርብ ሜይ 18 በ Ronald Regan Building, 14th St and Pennsylvania Av NW, 7 ኤ ኤም ላይ በመገኘት ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።

በጉባኤው ላይ የአሜሪካውን ፐሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡት የጋናው መሪ ጆን አታ ሚልስ፣ 99 ነጥብ 6 በመቶ አሸንፌ ተመርጫለሁ የሚሉት አቶ መለስ ዜናዊ፣ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የቤኒኑ መሪ ያይ ቦኒ፣ የታንዛኒያው መሪ ጃካያ ኪኪዌቴ፣ የአሜረካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፣ የአሜሪካ የውጭ ልማት ዋና ተጠሪ፣ ራጅቭ ሻህ፣ ታዋቂው አርቲስት ቦኖ ፣ የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኤርትሪን ከዚን እና ሌሎችም ባለስልጣናት ይገኛሉ።

ባራክ ኦባማ አቶ መለስን  በመጋበዛቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ ሰብአዊ መብት እና ዲሞክራሲን እንደሚያከብሩ የገቡትን ቃል አጥፈዋል በሚል እየተተቹ ነው። ባለፉት 20 አመታት ወደ ውጭ አገር በወጡ ቁጥር የተቃውሞ ሰልፍ ተለይቶዋቸው ከማያውቁ የአለም መሪዎች መካከል አቶ መለስ ዜናዊ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide