ኢሳት (የካቲት 17 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ካላት ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መካከል 67 ሚሊዮን የሚሆነው አስተማማኝ የኤለክትሪክ ሃይል አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆነ የአለም ባንክ ይፋ አደረገ።
ሃገሪቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶችን በመገንባት ላይ ብትሆም በአለም ደረጃ ለዜጎቿ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ማቅረብ ካልቻሉ ሃገራት ተርታ መመደቧን ባንኩ አዲስ ባወጣው ሪፖርት ማመልክተቱን ዘጋርዲያን የተሰኘ የናይጀሪያ አመልክቷል።
በአለማችን ህንድ ለ263 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ ባለመቻሏ በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠች ሲሆን፣ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ለ75 ሚሊዮን የሃገሪቱ ነዋሪዎች አገልግሎቱን መቅረብ ሳትችል መቅረቷን የአለም ባንክ በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።
ከአፍሪካ ከናይጀሪያ በመቀጠል ኢትዮጵያ ለ67 ሚሊዮን ዜጎቿ ይህንኑ አገልግሎት ማቅረብ እንዳልቻለች የተገለጸ ሲሆን፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ለ40 እና 33 ሚሊዮን ነዋሪዎቻቸው የኤሌክትሪክ ሃይሉን ማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአህጉሪቱ በናይጀሪያ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ብቻ 116 የሚሊዮን ሰዎች አገልግሎቱን የማያገኙ ሲሆን፣ ችግሩ በሃገራቱ ዜጎች ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ ስራውን የጀመረውን የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክትን በሃገሪቱ ወደ 3ሺ ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ማምረት እንደጀመረ ተገልጿል።
ይሁንና በመመረት ላይ ካለው ከዚሁ የሃይል አቅርቦት የተወሰነው ለጎረቤት ጅቡቲና ሱዳን በመቅረብ ላይ ሲሆን፣ ለሃገር ውስጥ ተጠቃሚዎች የሚቀርበው አገልግሎት አስተማማኝ አለመሆኑን የኢንቨስትመንት ተቋማትና ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ ባሉ ሃገራት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጄክቶች ቢከናወኑም አሁንም ድረስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሰረታዊ የሚባለውን አገልግሎት እንደማያገኙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ የአለም ባንክ ሪፖርትን ጠቅሶ አስነብቧል።
የመንግስት ባለስልጣናት የሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ሽፋን እስካለፈው አመት ድረስ 55 በመቶ መድረሱን መገለጻቸው ይታወሳል።
ይሁንና የሃገሪቱ የፍላጎትና የአቅርቦት ሁኔታ አሁንም ድረስ ሰፊ ልዩነት ያለው ሲሆን፣ መንግስት ክፍተቱን ለማጥበብ በርካታ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ስራ እየተካሄደ መሆኑን ይገልጻል።
6ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የአባይ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ለጎረቤት ሃገራት ሃይል እንደሚያቀርብ ይነገራል።
ይሁንና በመገንባት ላይ ያሉ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች የፋይናንስ እጥረት አጋጥሟቸው እንደሚገኝና የግንባታ መስተጓጎል መኖሩን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ሃላፊዎች በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ባለስልጣናቱ የትኞቹ ፕሮጄክቶች በገንዘብ እጥረት እክል እንዳጋጠማቸው ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።