46 ኢትዮጵያውያን በኤደን ባህር ላይ ህይወታቸው አለፈ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ/ም) ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት በምህጻረ ቃሉ -አይ ኦ ኤም እንዳስታወቀው ትናንት ረቡዕ 100 የሚሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው መርከብ በመስጠሟ፣ 37 ወንዶችና 9 ሴቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። 16 ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። በጀልባዋ ላይ የተሳፈሩት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ የገለጸው አይ ኦ ኤም፣ ከሶማሊያ የቦሳሶ ወደብ ተነስተው የመን ወደብ ሊደርሱ ጥቂት ኪሎሜትሮች ሲቀራቸው በማእበል እንደተመቱ አመልክቷል፤፡
በህይወት ከተረፉት መካከል አንዳንዶች ለድርጅቱ በሰጡት አስተያዬት ” ማዕበሉ እንደተነሳ አንዳንዶች መረበሽ ጀመሩ። ውሃ ወደ ጀልባው መግባት ሲጀምር በማእበሉ ተግፈተው ተወሰዱ “ብለዋል።
ከ7 ሺ በላይ ስደተኞች በየወሩ ወደ የመን አደገኛ የሆነ ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ባለፈው አመት ብቻ 100 ሺ ሰዎች ተሰደዋል።