435 ሺ ኢትዮጵያውያን ህጻናት በከፍተኛ ምግብ እጥረት ተጎድተዋል ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ውስጥ በበሽታ፣ በምግብ እጥረትና፣ በውሃ ጥማት ከተጋለጡት ከ6 ሚሊዮን ህጻናት ውስጥ፣ 435 ሺ የሚሆኑት በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።

የህፃናት በምግብ መጎዳት የአእምሮና እድገትን የሚጎዳና የማሰብ ችግር የሚያመጣ መሆኑን አቶ ሳሙዔል ተፈራ የተባሉ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ባለሙያን ጠቅሶ የአሜሪካ ድምጽ አገልግሎት የእንግሊዝኛው ክፍል ትናንት ሰኞ ዘግቧል።

አቶ ሳሙዔል የምግብ እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣዳፊ የተቅማት በሽታም ጭምር ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ለቪኦኤ አክለው ገልጸዋል።

በመተሃራ የሚኖሩ የሶስት አመት ልጅ እናት የሆኑትና ልጃቸውን ይዘው ወደክሊኒክ የመጡት ወ/ሮ ብሪቱ ሃዋስ የተባሉት ሴት ልጃቸው የታመመችበት ምክንያት የምግብ እጥረት ስላጋጠማት እንደሆነ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩም አልኮ ቡልቱ የተባሉት ሴት ለዚሁ የዜና አውታር እንደተናገሩት፣ 6 ልጆቻቸውን መመገብ የቻሉት በሚያገኙት እርዳታ ነው። “ከመንግስታት ዕርዳታ ውጪም ምንም የለንም ፥ በቤታችን ውስጥ የሚበላ ነገር የለም። ልጆቻችንን የምናበላው ምግብ የለም ፥ የምንጠጣው ውሃም የለም” በማለት የምግብ እጥረቱን አስከፊነት ተናግረዋል።

በመተሃራ አካባቢ፣ ተማሪዎችም አንዳንድ ስራዎች በመስራት ወላጆቻቸውን ለማገዝ ትምህታቸውን ማቋረጣቸው ተነግሯል። በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚውል “ቻይልድ ፈንድ” የተባለ ድርጅት ወደ 800 ሚሊዮን የረዳ ቢሆን፣ የተባበሩት መንግስታት እና የኢትዮጵያ መንግስት በበኩላቸው ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል። አብዛኛው ገንዘብም ለምግብ አገልግሎት እንደሚውል ታውቋል። የተረጂዎች የምግብ ፍላጎትም እኤአ እስከ 2017 ዓም ድረስ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።