የዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆኖ በመመረጡ ደስታቸውን የገለጹ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተደበደቡ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) የኦህዴዱ ሊ/መንበር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይፋ እንደሆነ ደስታቸውን በመግለጽ ላይ የነበሩ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ በአጋዚ ወታደሮች ከፉኛ መደብደባቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ትናንት ፣ ረቡዕ፣ በኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች፣በድስታ ሲጨፍሩ ኮማንድ ፖስት ሳታስፈቅዱ ለምን ጨፈራችሁ በሚል በከፍተኛ ሁኔታ እንደደበደቡዋቸውና ብዙዎች እንደተጎዱ ታውቋል።
በአካባቢው የነበሩ የኮማንድ ፖስት አዛዦች በዶ/ር አብይ መመረጥ ደስተኛ አይደሉም ያሉት ተማሪዎች፣ ብስጭታቸውን ተማሪዎችን በመደብደብ እንደተወጡት ገልጸዋል።
የዶ/ር አብይ መመረጥ ይፋ እንደተደረገ፣ በጉጂ እና በቦረና ዞኖች ህዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታውን ጥይት በመተኮስ ጭምር ሲገልጽ፣ ወታደራዊ አዛዦች ምንም እርምጃ እንዳልወሰዱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች ባለቡትና የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳር ባልሰፋበት ወቅት የሚመረጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር የሃገሪቱን አንድነት አስጠብቀው ለመጓዝ ፈታኝ መሰናክሎችን ማለፍ እንዳለባቸው በአማራ ክልል የሚገኙ ምሁራን ገልጸዋል።
ሃገሪቱ በከፋ ሁኔታ የገጠማትን የመልካም አስተዳደር ችግር አለመፍታቷ የቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተግዳሮቶች እንደሆኑ የሚናገሩት ምሁራን፣ ሃገሪቱን ካለችበት ችግር ለማውጣት ግለሰብ መቀያየር ሳይሆን ሃገራዊ እርቅ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ለመጓዝ በውጭና ሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማሳተፍ የጋራ መድረክ በመምረጥ ሃገራዊ ዕርቅ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
ምሁራኑ፣ ኢህአዴግ ቀደም ሲል በነበረው ፖሊሲ ፣ስትራቴጂና አሰራር የሚቀጥል ከሆነ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ተናግረው፤ በዚህ አሰራር ሰው ተነስቶ ሰው መተካቱ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም።
ገዥው መንግስት ከህገመንግስቱ ጀምሮ መስተካከል የሚገባቸውን በማስተካከል ፣የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ በሃገር ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሳተፍ፣ አዲስ ስራ መስራት ካልተቻለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ብቻቸውን ምንም ለውጥ ማምጣት አይችሉም ሲሉ ያስረዳሉ።
ገዥው መንግስት በአሸባሪነት የፈረጃቸውንና በትጥቅ ትግሉ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ወገኖች ጋር በመነጋገር የጋራ የሆነቸውን ሃገር በጋራ ለማዳን የሚያስችለውን መድረክ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሊፈጥሩ እንደሚገባም ምሁራኑ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ አርበኞች ግንቦት7 ባወጣው መግለጫ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ሃይሎችም ሆኑ ዶ/ር አብይ ስለሚወስዱዋቸው እርምጃዎች ዘርዝሮ አቅርቧል። “የዶ/ር አብይ መመረጥ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት እስካሁን የህወሀት ሎሌ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ድርጅቶችና በህወሓት ውስጥም ያሉ አንዳንድ ለውጥ ፈላጊዎች በጋራ አሸንፈው ከሆነና እነ ዶ/ር አብይ በተለይ በኦህዴድ ምክር ቤት ስብሰባ መግለጫ ላይ ያወጡትን ለውጥ ፈላጊ አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነው ከሆነ እሰየው ነው” ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል፣ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ብሎም ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለውጥ ፈላጊው ህዝብ ሁሉ የሚፈልገው ነውና በአዎንታዊ መልኩ እወስደዋለሁ ብሎአል።
ዶ/ር አቢይ ስልጣኑን ከተረከቡ እለት ጀምሮ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት የመጀመሪያ ስራቸዉ መሆን አለበት ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ መወሰድ አለባቸው ያላቸውን እርምጃዎችም ዘርዝሮ አቅርቧል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍታት፣ ህገ-ወጡን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማንሳት፣ በህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በአስቸኳይ ማስቆምና ለዚህ ዕርምጃ ዋስትና እንዲሆን የአገሪቱን የደህንነት ተቋሞች እንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀር፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታገዱ ያደረጋቸዉና አዋጁ ከመታወጁ በፊትም ቢሆን በፍጹም ተከብረዉ የማያዉቁትን መደራጀትን፣ መሰብሰብን፣ መቃወምን፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የህግ የበላይነትን የመሳሰሉ መሠረታዊ የሰዉ ልጅ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ኢትዮጵያን ወደ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መውሰድ የሚችል ሁሉን አቀፍ ውይይትና የሽግግር ሂደት በአስቸኳይ ማስጀመር” የሚሉት እርምጃዎች በመግለጫው ከተጠቀሱት ዋነኞቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝብ የሚፈልገዉ ለዉጥ በተለያየ መልኩ ሊመጣ እንደሚችልና ለውጥ ከየትም ይምጣ ከየት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን በደስታ እንደሚቀበል የገለጸው አርበኞች ግንቦት7፣ ነገር ግን ከእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ውጭ የሆነ ምንም አይነት ጥገናዊ ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኑን ገልጿል።
ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚወስደን የሽግግር ሂደት ተጀምሮ ህዝባዊ ትግሉ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱ እስከሚረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረዉን የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል ለአንድም ቀን ቢሆን እንዳያቆም አርበኞች ግንቦት 7 አሳስቧል።