ዘጠኝ የአገዛዙ ታጣቂዎች በአንድ የአካባቢው ሰው መቁሰላቸው ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2010) በምዕራብ ጎጃም በደቡብ አቸፈር ወረዳ ዱርቤቴ ከተማ ዘጠኝ የአገዛዙ ታጣቂዎች በአንድ የአካባቢው ሰው መቁሰላቸው ተሰማ።

በዱርቤቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና አቶ ደርቤ አየለ የተባሉ የአካባቢው ታዋቂ ሰው በፌደራል ሰዎች ተከበው እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተኩስ መጀመሩ ተነግሯል።

አቶ ደርቤ በከበቧቸው የአገዛዙ ታጣቂዎች ላይ የአጸፋ ርምጃ በመውሰድ ከ9 በላይ ወታደሮች አቁስለዋል።ከቆሰሉት መካከል የሞቱ እንዳሉም ይነገራል።

በመጨረሻም አቶ ደርቤ እጄን አልሰጥም በማለት ራሳቸውን እንዳጠፉም ለማወቅ ተችሏል።

የነገሩ መነሻ በውል አይታወቅም።

የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት ግን ጉዳዩ ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም።

አቶ ደርቤ አየለ ይባላሉ።በምዕራብ ጎጃም ዱርቤቴ ከተማ የሚኖሩና በአካባቢው ሰው በጀግንነታቸው የሚታወቁ ሰው ናቸው።

እናም ድንገት በተፈጠረ የቤተሰብ ግጭትና አለመግባባት ብቻ በኮማንድ ፖስቱ ይከበባሉ።–እጃቸውንም እንዲሰጡ ይጠየቃሉ።

በርካታ የአገዛዙ ወታደሮች ከባህርዳር ሳይቀር በመምጣት ቤታቸውን ቢከቡም አቶ ደርቤ አየለ ግን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በዚህ መሃልም ተኩስ ተከፈተባቸው።እሳቸውም የአጸፋ ምላሽ ሰጡ።

የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት አቶ ደርቤ አየለ እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ተከታታይ የእጅ ቦምቦችን በኮማንድ ፖስቱ ላይ መወርወራቸው ታውቋል።

በእጃቸው የነበረውን መትረየስ መሳሪያ በመጠቀምም ብዙ ወታደሮችን አቁስለዋል።

9 የአገዛዙ ወታደሮችም ቆስለው ወደ ባህርዳር ሆስፒታል ተወስደዋል ነው የተባለው።–ከቆሰሉት መካከል የሞቱም እንዳሉ ነው ከስፍራው የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው።

በመጨረሻም አንድ ሆነው ብዙዎቹን የአገዛዙ ወታደሮች ከረፈረፉ በኋላ አቶ ደርቤ አየለ የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋታቸው ተሰምቷል።

በቤተሰብ ጉዳይ በኮማንድ ፖስቱ የተከበቡት አቶ ደርቤ አየለ በፎቶግራፍ ስራ የሚተዳደሩና የቀድሞ የደርግ ወታደር እንደነበሩ ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል።