(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2010)
በአዲስ አበባ በሳህሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ዳግም ግጭት ተቀሰቀ።
በቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ የድረሱልን የደወል ድምጽ በመሰማቱ በርካታ ምዕመናን በአካባቢው ተገኝተው የተቃውሞ ድምጽ ማሰማታቸው ታውቋል።
ለተቃውሞው ምክንያት የሆነው የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ድብደባ ደርሶባቸው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ተመልሰው ወደ መቅደስ እገባለሁ በማለታቸው ነው።
ቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት መከበቧም ተነግሯል።
በሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ምዝበራ እየተፈጸመ ነው በመባሉ ምዕመናኑ ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የቤተክርስቲያኗ አስተዳደሪ የንበሩት የሕወሃት አባል ኣንደሆኑ የሚነገርላቸው መልዓከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ቢከለከሉም በሃይል እገባለሁ ሲሉ ባለፈው ሳምንት ተደብድበው ሆስፒታል ገብተው ነበር።
ይህንንም ባለፈው ሰኞ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
ዛሬ አስተዳዳሪው ከሆስፒታል መልስ ወደ ቤተመቅደስ ገብቼ እቃ አወጣለሁ በማለታቸው የቤተክርስቲያን ደውል ተደውሎ ለሕዝቡ ጥሪ በመደረጉ በአካባቢው ብጥብጥ ተፈጥሯል።
ሕዝቡ ተቃውሞ እያሰማ በነበረበት ጊዜ የቤተክርቲያኒቲ የልማት ክፍል ጸሃፊ ሊቀ አእላፍ እጹብ የማነብርሃን፣ሒሳብ ሹም ሊቀ ትጉሃን ዘርአ ብሩክ አብርሃ ያለሰበካ ጉባኤ ውክልና ምክትል ሊቀመንበር ነኝ የሚለው ቀሲስ ካሳሁን ገብረሕይወት በግቢው ውስጥ ታግተው መቆየታቸው ነው የተገለጸው።
በሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን በልማት ስም የተገነቡ በግቢው ዙሪያ ያሉ የንግድ መደብሮች በአብዛኛው በትግራይ ተወላጆች የተያዙ መሆናቸው ታውቋል።
ሕዝቡ አስተዳዳሪውን ሌባና ዘራፊ ስለሆንክ ወደ ቤተክርስቲያናችን በግባት አትችልም በማለቱም የፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በማምራት ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ ያልበገረው ሕዝብ ግን ወያኔ ሌባ በማለት ተቃውሞውን ሲገልጽ እንደነበር ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።
የሕዝቡ እንቅስቃሴ ያስፈራው የሕወሃት መንግስትም ከመገናኛ ወደ ሲ ኤም ሲ የሚወስደውን መንገድ ዘግቶ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል።