ኢሳት (የካቲት 17 ፥ 2009)
ንብረትነቱ የሳውዲ አረቢያ በሆነ አውሮፕላን በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ነበር የተባለ ከ300 ኪሎግራም በላይ የዝሆን ጥርስ በአዲስ አበባ ቦሌ አውርፕላን ማረፊያ ጣቢያ አርብ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የዝሆን ጥርሱ ከናይጀሪያ ተነስቶ ወደ ምዕራባዊያን አፍሪካዊት ማሊ ሊጓጓዝ እንደነበር የኢትዮጵያ ገበዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል። ይኸው ድርጊት ከህግ ጥሰት ባሻገር በኮንትሮባንድ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በሳውዲ አረቢያ አየር መንገድ ላይ ምን አይነት ክስ እንደሚመሰረት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ 302 ኪሎግራም በሚመዝነው የዝሆን ጥርስ በቦሌ አውሮፕላን በአንድ ጊዜ ሲያዝ መጠኑ የመጀመሪያው መሆኑም ታውቋል።
የዝሆን ጥርስ ዝውውር በአለም አቀፍ ደረጃ ከሃያ አመት በፊት እገዳ እንደተጣለበት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዝሆን ጥርሱ ዝውውር በአለም አቅፍ ደረጃ እገዳ ቢጣልበትም የተለያዩ ግለሰቦች ለተያዩ ጌጣጌቶጭ የሚለውን ይህንኑ ጥርስ በህገወጥ መንገድ ለማዘዋወር በሞከሩ ጊዜ የእስር ቅጣት እየተላለፈባቸው ይገኛል።
በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ከዋለው የዝሆን ጥርስ ጋር በተገኛኘ ለእስር የተዳረገ ሰው ይኑር አይኑር የተገለጸ ነገር የለም።
የአንድ ኪሎግራም የዝሆን ጥርስ በትንሹ እስከ ሁለት ሺ የአሜሪካን ዶላር በህገወጥ መንገድ እንደሚሸጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።