ኢሳት (ታህሳስ 24 ፥ 2009)
የአንጋፋው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የቀብር ስነስርዓት እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ በመንበረ-ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ በርካታ የአትሌቱ ደጋፊዎችና ቤተሰቦች እንዲሁም መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮች በቀብር ስነስርዓቱ መታደማቸው ታውቋል። ዕሁድ ከሰዓት በተፈጸመው በዚሁ የቀብር ስነስርዓት ወቅት ለአትሌቱ ክብር ሲባል ዘጠኝ ጊዜ መድፍ መተኮሱ ታውቋል። በዚሁ ዝግጅት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የሃገሪቱን ብሎም የአፍሪካን ስም በአለም ለማስጠራት ያደረገው ጥረትም በሰፊው ቀርቧል።
ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ኦሎምፒክን ጨምሮ በተለያዩ አለም አቅፍ ውድድሮች ለኢትዮጵያ ሜዳሊያዎችን በማስገኘት አስተዋጽዖን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ300 በላይ ውድድሮችን አድርጎ በ271 ዱ ድል ማድረጉ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።
በ72 አመቱ ከዚህ አለም የተሰናበተውና በአሯሯጥ ጠበቡ ማርሽ ቀያሪው የሚል መጠሪያ ያለው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በሚኖሩበት ካናዳ ባጋጠመው የጤና አክል ባለፈው ሳምንት ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
መኖሪያቸው በካናዳ የሆኑ ኢትዮጵጵያውያን የአትሌቱ አስከሬን ወደ ሃገር ቤት እንዲጓጓዝና በቆይታውም የሽኝት ስነ-ስርዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ ትብብሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ስንዘግብ መቆየታቸው ይታወቃል።
ዕሁድ ጠዋት አስከሬኑ አዲስ አበባ የደረሰው ሻምበል ምሩፅ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች የአሸኛኘት ስነስርዓት ተካሄዶለት የቀብር ስነስርዓቱ አድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በክብር መከናወኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።