ኢሳት (ታህሳስ 24 ፥ 2009)
በነጻ በተሰናበቱ ጦማሪያን ላይ የቀረበለትን የይግባኝ ጥያቄ በመመልከት ላይ የሚገኘው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሟላ ማስረጃ እንዳልቀረበለት ገለጸ። በዚሁ ውሳኔ ለማሳለፍ መቸገሩን ገልጿል።
በከሳሽ አቃቤ ህግ የቀረበለትን የይግባኝ ጥያቄ በመመልከት ላይ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ በታችኛው ፍርድ ቤት እንዳቅረባቸው በይግባኙ የገለጸው የሰነድና የሲዲ ማስረጃ ሊያገኝ አለመቻሉን እንዳስታወቀ ሪፖርተር አዲስ አበባ ላይ ዘግቧል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሽብርተኛ ወንጀል ተከሰው የቀረቡ የአራት ጦማሪያንን ጉዳይ ከመረመረ በኋላ ክሱን ውድቅ በማድረግ ተከሳሾቹን በነጻ ማሰናበቱ ይታወሳል።
ይሁንና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ከሳሽ አቃቤ ህግ ያቀረብኳቸው የክስ ማስረጃዎችን በአግባቡ ሳይታዩ ነው ተከሳሾች በነጻ የተሰናበቱት ሲል ይግባኙን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ይገኛል።
ሰሞኑን ይግባኙን የተመለከተው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠው ማስረጃውን መርምሮ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማየትና ውሳኔ ለመስጠት መቸገሩን ያስታወቀ ሲሆን፣ በይግባኝ ጥያቄው የተገለጸው የሰነድና የሲዲ ማስረጃ ሊያገኝ አለመቻሉንም አመልክቷል።
በጦማሪያኑ አቃቤ ህግ አለ የሚለው ሲዲ እነሱን የሚመለከት ማስረጃ አይደለም በማለት ለችሎት ገልጸዋል። ሲዲውን አንደኛ ተከሳሽን የሚመለከት መሆኑን አቃቤ ህግ ለታችኛው ፍርድ ቤት አስረድቶ እንደነበር ጦማሪያኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አውስተዋል።
በቀረበባቸው ይግባኝ ምክንያት እንደልብ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የገለጹት አራቱ ጦማሪያን ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም አቃቤ ህግ አለኝ ያለውን ሲዲና ማስራጃውን ለጥር 19, 2009 አም እንዲያቀርብ ትዕዛዝን የሰጠ ሲሆን፣ ጦማሪያን ሶሊያና ሽመልስ፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ናትናዔል ፈለቀ፣ አቤል ዋቤላና አጥናፍ ብርሃኔ በዚሁ ይግባኝ ጉዳያቸው በመታየት ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።