ነሃሴ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት አለም አቀፍ የምግብ ድርጅት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተለያዩ ግጭቶችና አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው 250 ሺህ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ መስጠት መጀመሩን ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ በኦሮሚያና አማራ ደርሶ ስለነበረው ግጭት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ቢቆጠብም 250ሺህ ለሆኑት ዜጎች ግን ጊዜያዊ የሆነ የምግብና የገንዘብ እርዳታ መስጠት ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ከአውሮፓ ህብረት ሰብዓዊ እና ሲቪል ዜጎችን መከላከል ተቋም በተገኘ እርዳታ ጊዜያዊው እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የተባበሩት የአለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አብዱ ዲያንግ ተጎጂ ዜጎቹ በአሁኑ ሰዓት እንደሚኖሩበት አካባቢ የገበያ ሁኔታ በነፍስ ወከፍ በወር 150 ብር ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሰብዓዊና ሲቪል ዜጎችን መከላከል ተቋም ዜጎቹን በጊዜያዊነት ለመርዳት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡ በኦሮሚያና አማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች መብታቸውን ለመጠየቅ ባደረጉት እንቅስቃሴ በደረሰባቸው የመንግስት እርምጃ በርካቶች መፈናቀላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያ ወደ የመን የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር መንግስት አልባ ተደርጋ ከምትቆጠረው ሶማሊያ በመብለጥ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቡን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 38 ሺህ 824 ኢትዮጵያን (ማለት ከጠቅላላው 84 ፐርሰንት) የሆኑ ዜጎች መሰደዳቸውን ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት 7ሺህ 559 ሶማሌያን እና 17 ኤርትራውያን ብቻ ወደ የመን መግባታቸውን ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በየመን ከደረሱት ኢትዮጵያውያን ውስጥ በጣም ጥቂት የሆኑት ብቻ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ የተቀሩት ግን በመረጃ እጦትና የተለያዩ ችግሮች ለችግር መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት 46 ሺህ ስደተኞች ወደ የመን አስቸጋሪ ጉዞ አድርገው መግባታቸውን ገልጾ ከነዚህ ውስጥ 38ሺህ 824ቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ከፈረንጆቹ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ወደ የመን መሰደዳቸውን የገለጸው ድርጅቱ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ቀይ ባህርን በአነስተኛ ጀልባዎች በመጠቀም ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በዓመት ወደ 80 ሺህ እንደሚጠጋ ሰሞኑን ቢቢሲ ለአለም ባሰራጨው ዶክመንተሪ ፊልም መታየቱ ይታወሳል፡፡
ከሚሰደዱት ሴቶች አብዛኛዎቹ የመደፈር አደጋ የሚደርስባቸው ሲሆን በርካታ ዜጎችም በቀይ ባህር ላይ በመስመጥ መሞታቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡