ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2008)
በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ትናንት ሰኞ ከባድ ዝናብ ጥሎ ከ400 ሰዎች በላይ ሲፈናቀሉ፣ አገልግሎት ድርጅቶች መውደማቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ገለጹ። በከተማው 03 ፥ 02 እና 05 ቀበሌ በደረሰው በዚሁ የጎርፍ አደጋ፣ በርካታ የንግድ ሱቁችና ሆቴሎችና የህክምና ተቋም በጎርፉ ተወስደዋል።
በደረሰው ጎርፍ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም፣ የንግድ ሱቆችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በጎርፍ ፈራርሰው ተወስደዋል። በጎርፍ ከተወሰዱት የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና የግለሰብ ቤቶች በተጨማሪ፣ ይፋት የተባለ ሆስፒታል በጎርፉ የተጎዳ ሲሆን፣ በውስጡ የነበሩ መገልገያ ዕቃዎች በአብዛኛው በጎርፉ አደጋ መወሰዳቸው ተነግሯል።
በዚሁ የጎርፍ አደጋ በአራት ቀበሌዎች የሚኖሩትና ከቀያቸው የመፈናቀል አደጋ የደረሰባቸው ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረትም መውደሙ የከተማው አሰተዳደር ገልጿል።
ጎርፉ እንደደረሰ የቴሌኮሚውኒኬሽን ኔትወርክ የጠፋ ሲሆን፣ የጎርፉ አደጋ ዜና ለመገናኛ ለብዙሃን እንዳይደርስ ሆን ተብሎ የተሰራ ደባ ሊሆን እንደሚችል በስፍራው የነበሩት የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
ጎርፉ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው የቆቦ ጅረት ድልድይ ሳይጠገን በመቅረቱና፣ ጎርፉ አቅጣጫውን ስቶ በከተማ ባሉ በንግድና መኖሪያ ቤቶች በመግባቱ መሆኑ ታውቋል።
በቅርቡ በጅማ ከተማ ደርሶ በነበረ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውም ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተያዘው የፈረንጆች አመት ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ሰዎች በሃገሪቱ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው በመግለጽ የቅድመ መከላከል ስራ እንደሚካሄድ ማሳሰቡ ይታወሳል።